የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና በርካታ ወጣቶችን ለማፈን የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው

ጥቅምት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አገሪቱ በአንድ ወታደራዊ እዝ ስር መውደቋ በተነገረ ማግስት፣ አገዛዙ የተቃዋሚ መሪዎችን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን መርተዋል፣ አስተባብረዋል እንዲሁም ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች እየተያዙ ወደ እስር ቤት እየተላኩ ነው።

በመላው አገሪቱ የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩት አፈናው በመላ አገሪቱ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በርካታ ወጣቶች አፈናውን በመፍራት ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች በመሸሽ ላይ ናቸው ። ሌሊቱን በጫካ የሚያሳልፉ ወጣቶችም አሉ።

በምዕራብ ጉጂ ዞን በገላና ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ በድሉ መንግስቱ ለስራ ጉዳይ ከከተማው እንደወጡ ወታደሮች ባለቤቱን ወ/ሮ ምስራቅ አሰፋን ከቤት አስወጥተው ቤቱን ፈትሸውበታል። ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡም አሰደርገዋል ።

በኦሮምያ፣ በደቡብና በአማራ ክልል የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ቤቶቻቸው በድንገት እየተሰበሩ እየተፈተሹባቸው ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ገዢው ፓርቲ አሁንም የሳተላይት ዲሽ ማስወረዱን ቀጥሎበታል። ህዝቡ ኢሳትን ጨምሮ ከውጭ የሚተላለፉ ዜናዎችን እንዳይመለከት ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠንከሮ ሊቀጥል እንደሚችል እና ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በየአካባቢው የሚገኙ ወኪሎቻችን ምክራቸውን ለግሰዋል።

በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመዝጋት የሚያደርጋቸው አፈናዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና ስራ መስራት ከባድ እየሆነ መምጣቱን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሜቴ ታይጌሰን አስታውቀዋል።

ከኢሬቻ በዓል ግድያ በኋላ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ አገዛዙ  የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ዝግ አድርጓል።በኢትዮጵያ አንድ ዓመት በዘለቀው ሕዝባዊ እንቢተኝነት በዐማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተቃውሞዎች ሲነሱ በተመሳሳይ የኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ የማኅበራዊ ድረገጾች አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።

በዴንማርክ የጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ተወካይ የሆኑት ሜቴ ታይጌሰን እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት የሞባይል ኢንተርኔት እና ማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመልስ አሁንም ድረስ ፈቃደኝነቱን አላሳየም ።