ሚያዝያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጅማ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑ በተደረገ አውደጥናት ላይ ፣ በየዓመቱ በየጊዜው የሚቀያየረው የትምህርት ፖሊሲ ርእይ ያለው ወጣት እንዳይፈጠር ማድረጉ ተገልጿል ፡፡ ሀገሪቱ ወጥ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ ይዛ ባለመማራቷ
ችግሩ መፈጠሩንም ምሁራን ተናግረዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የቻሉ ብዙ ተማሪዎች በምደባ ከፍላጐታቸው የራቀ ትምህርት እንዲያጠኑ በመደረጉ በአመት ከ12 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በውጤት መበላሸት ይባረራሉ፡፡
እየከሸፈ ባለው የትምህርት ፖሊሲ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ 70 በ 30 ማለትም 70 በመቶ ተማሪዎች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎችን እንዲያጠኑ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎችን እንዲያጠኑ ከተደረገ በኋላም
ተማሪዎች ባላሰቡት የትምህርት ክፍል መገኘታቸው ችግሩን አባብሶታል።
የተማሪዎችን ፍላጐት አለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን እየተመደቡ ያሉት ተማሪዎች ስሙን እንኳ ሰምተውት በማያውቁት የትምህርት መስክ ወይም ዲፓርትመንት መሆኑ፣ ለውዝግብ መነሻና ለዲፓርትመንቶች መዘጋት ምክንያት ሆኗል።
ከ2001 -2007 ዓ.ም ባሉት አመታት በቀደምት ዩኒቨርስቲዎች 63 አይነት የትምህርት መስኮች ተከፍተው ከሀገሪቱ የስራ ቦታ ፍላጎት ጋር ባለመጣጣማቸው ተዘግተዋል፡፡
በኮርስ ስም ሳይቀር የትምህርት ክፍል ወይም ዲፓርትመንት የሚከፍቱ ዩኒቨርስቲዎች መፈጠራቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡ ጅማ ፣ መቀሌ ፣ ባህርዳር እና ሀዋሳ ዩኒቨርስቲዎች በየጊዜው አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን ከፍተው የሚዘጉ ተቋማት ናቸው ተብሎአል፡፡
ለምሳሌ ያክል ይላሉ ጥናት አቅራቢዎች የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አግሪ ካልቸራል ሪሶርስ በአግሪካልቸራል ሪሶርስ ሥር ከሚገኙ ባዮቴክኖሎጂ ፣ሆርቲካልቸር፣ ዋተር ሪሶርስና ኢሪጌሽን ፤ ፊሽሪ ፤ ዋተር ዲቨሎፕመንት እና በአጠቃላይ ከአሥራ አምስት ዲፓርትመንቶች አንዱን
እንኳን የመንግስት ስራ ቀጣሪው ሲቪል ሰርቪስ አያውቀውም ፡፡
በአገሪቱ ያለው የሰው ሃይል ገበያ የሚዘጉና የሚቀጥሉትን ዲፓርትመንቶች ይወስን የሚለው ፖሊሲ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና፣ታሪክና ጂኦግራፊ ዲፓርትመንቶች የተማሪዎች ቁጥር እንዲያሽቆለቁል መደረጉም ተወስቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝም መምህር የሆኑት ዶ/ር አብዲሳ ‹‹ለተማሪዎች እያስተላለፍን ያለነው የገበያን የዋጋ እሴት ነው፡፡የሰው ልጅ በዕውቀት የመበልፀግና ምሉዕ የመሆን ነገር ዋጋ አልተሰጠውም፡፡ የሚጠየቀው ሥርዓተ ትምህርቱ በገበያ ዋጋ ስንት
ያወጣል? ተብሎነው›› ሲሉ ትችት አቅርበዋል።
የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ታምራት 70 በ 30 የሚለውን የትምህርት ፖሊሲው ጥመርታ በየግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተፈፃሚ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል።
የግል ተቋማቱ ገንዘባቸውን ከፍለው ምናልባትም ሙያቸውን ለማዳበር ማጥናት የሚፈልጉትን የወሰኑ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ በመሆናቸው ፖሊሲውን ተፈጻሚ ማድረግ አይቻልም።
‹‹ተማሪዎቹ በገንዘባቸው የሚያዙ እንደመሆናቸው የምመርጥልህን ነው የምትማረው ቢባሉ ነገሩ የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ በጥመርታው መሠረት 70% በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተማሪዎችን እንቀበል ብለን በሰው ኃይል በሌላም በሌላም ብንዘጋጅ በዝግጅታችን
መሠረት ተማሪዎች ባይመጡ ትልቅ ኪሳራ ይፈጠራ ሲሉ አክለዋል።
በ2011/ 2012 ብቻ 400 የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት መምህራን ወደ ውጭ ሐገር ለትምህርት ሂደው በተለያየ ምክንያት ጥገኝነት ጠይቀው በዚያው ቀርተዋል።
ጅማ፣ መቀሌ እና ባህርዳር ዩኒቨርስቲዎች በምሁራን ፍልሰት ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ 673 ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መምህራንም ስራቸውን ጥለው ወጥተዋል።
በቂ ክፍያ ያለመኖር፣ የፖለቲካ ጫናዎች መበራከት፣ከትምህርት ጥራት ይልቅ ለትምህርት ሺፋን ትኩረት መስጠት፤ መምህራን ያለ እምነታቸው በግዳጅ የሚፈጽማቸው ስራዎች መበራከት፤ ለመምህራን ፍልሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።