የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ማጣራት እንዲደረግበት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተወያየ እንደሆነ ገለጸ

ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ማጣራት እንዲደረግበት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ረቡዕ ይፋ አደረገ።

በአለም ዙሪያ የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከታተለው ይኸው አካል የኢትዮጵያ  መንግስት ከአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል በሯን ክፍት እንድታደርግ በይፋ መጠየቁን ሮይተርስ ከጄኔቭ ዘግቧል። UN HR

ከቀናት በፊት ከ100 ለሚበልጡ ሰዎች ግድያ ምክንያት የሆነው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫን የሰጡት የኮሚሽኑ ሃላፊ ዘይድ ራድ አል ሁሴን በሁለቱ ክልሎች በሳምንቱ መገባደጃ የተፈጸሙ ግድያዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት በድርጊቱ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሃላፊው፣ ይህንኑ ዘመቻ ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግድያውን ማጣራት እንዲካሄድበት መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት ዘልቆ ከቆየው ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በተመሳሳይ ሁኔታ ግድያ ተፈጽሞ በገለልገኛ አካል ማጣራ አለመካሄዱን ያወሱት የሰብዓዊ መበት ኮሚሽኑ ሃላፊ በሃገሪቱ በአጠቃላይ ስለተገደሉ ሰዎች ቁጥር ትክክለኛ መረጃ አለመገኘቱን አክለው አስታውቀዋል።

ከተቃውሞው ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋናው ጽ/ቤቱ ከሚገኝበት ጄኔቭ ከተማ ጥሪውን አቅርቧል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ከተለያዩ አካላት የሰበሰባቸውን ማስረጃዎች ዋቢ በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በቅርቡ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችም ለእስር መዳረጋቸው አመልክቷል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማጀብ የሚሰሩ የጸጥታ ሃይሎች ለግድያ የሚያበቁ መሳሪያዎችን መጣጠቅ እንደሌለባቸው አክሎ አሳስቧል።

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት በክልሉ የተፈጸመውን ግድያ በአለም አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ማጣሪያ እንዲካሄድበት ማሳሰቡ ይታወሳል።

የህብረቱ ፓርላማም የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አቋም እንዲያስተካክልና ዕርምጃን ለመውሰድ የሚያስችለውን የውሳኔ ሃሳብ ከወራት በፊት ማፅደቁ የሚታወስ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦችም ተመሳሳይ ጥያቄን እያቀረቡ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።