(Aug. 27) የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እስራት፤ መንግስት የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች የጥቃት ኢላማ ማድረጉን እንደሚቀጥልበት ጠቋሚ ነው፤ ሲል አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስጋቱን ገለጠ።
አቶ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ሀሙስ መታሰሩ የሚያሳየው ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላም ኢትዮጵያ ውስጥ ነገሮች እንዳልተቀየሩ ነው ሲሉ ክሌር ቤስተን የአምነስቲ አለማቀፍ የኢትዮጵያ ተመራማሪ ተናግረዋል።
ተመስገን የታሰረው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቱን ሲጠቀምና ሰላማዊ ትግልን ሲያራምድ መሆኑን የተናገሩት ክሌይር ቤስተን፤ ልክ የአቶ መለስ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ነጻ ሚዲያን ሽባ በማድረግና፤ ከስርአቱ የተለዩ ሀሳቦችን የሚያራምዱትን በማጥፋት እንደሚታወቀው፤ የተመስገን መታሰርም የሚያሳየው ነገሮች በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ ይደርጉ ከነበረበት ምንም እንዳልተለወጡ ነው ብለዋል።
በተያያዘ ዜና፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በአስቸኳይ እንዲፈታ አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት፤ በእንግሊዘኛው ኮሚቴ ቱ ፐሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) ጠየቀ።
ተመስገን ደሳለኝ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲታሰር 9ኛ ጋዜጠኛ ሲሆን፤ ተመስገን ወንጀለኛ ሳይሆን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕገመንግስታዊ መብቱን የሚጠቀም ጋዜጠኛ በመሆኑ፤ ክሱ ተጥሎ በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈታ ሲፒጄ ጠይቋል።
ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው አመት በጻፋቸው ጽሁፎች፤ ሕገመንገስቱን በመጻረር ወጣቶችን ለአመጽ እንዲነሳሱ በመቀስቀስ፤ የመንግስትን ስም ጥላሸት በመቀባትና ህዝብን ማሳሳት በሚሉ ክሶች የተከሰሰ ሲሆን፤ ባለፈው ሀሙስ ያስቻለው የከፍተኛው ፍ/ቤት፤ ተመስገን ደሳለኝን የዋስ መብት በመንፈግ ወደቃሊቲ እስር ቤት እንደላከው ታውቋል።
ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ግንቦት ከነእስክንድር ነጋ የፍረድ ሂደት ጋር በተያያዘ በጻፈው ጽሁፍ ምክንያት በ2000 ብር መቀጣቱና የአራት ወራት እግድ እስራት እንደተፈረደበት ይታወሳል።