የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞች ቃል የተገባላቸው የዲያስፖራ አባላት አዲስአበባ እየገቡ ነው

ሐምሌ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን አባላትን በቀላሉ ለመያዝ እንዲመች በሚል ስሌት የዲያስፖራ ቀን በኣል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በበአሉ ላይ ለሚገኙ የዲያስፖራ አባላት የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞች እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል።
ከሰሜን አሜሪካ የመጡ የኦሮሞ ተወላጆች ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት “በበዓሉ ላይ ከተገኙ በመረጡት አካባቢ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ወዲያውኑ ከሊዝ ነጻ እንደሚሰጣቸው፣ ወደኢንቨስትመንት የሚገቡ ከሆነ ደግሞ የሥራ ቦታና የባንክ ብድር እንደሚመቻችላቸው ቃል በተገባላቸው መሰረት” መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህው ከነሐሴ 6 እስከ 10 ቀን 2007 ዓ.ም በአዲስአበባ ለማካሄድ የታቀደው የዲያስፖራ በዓል ከፍተኛ ወጪ የተመደበለት ሲሆን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሰረት 6ሺ ገደማ ኢትዮጵያዊያን ይገኛሉ ተብሎአል፡፡
ሰሞኑን በተከናወነው የኦሮሚያ ተወላጆች የዲያስፖራ አባላት በዓል ላይ ቁጥራቸው 1ሺ የሚገመቱ ሰዎች ከውጭ ሀገር ገብተው በበዓሉ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ወገኖች የተገባላቸውን ቃል በቅርቡ ይፈጸምልናል ብለው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለአባይ ግድብ የዲስፖራ አባላት መዋጮ ሳያቋርጡ እንዲያዋጡና በልማትና ኢንቨስትመንት ሰበብ የውጭ ምንዛሪ ወደሀገር ውስጥ ይዘው እንዲገቡ በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ በተደጋጋሚ ያካሄደው ቅስቀሳ ሳይሳካ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የዲያስፖራ ቀን በሚል በአል የተዘጋጀው ዲስፖራውን ለመሳብ ድጋሜ ሙከራ ለማድረግ ሲሆን፣ አዲሱ ስልትም ረጅም ርቅት እንደማይሄድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደጠቆመው በበዓሉ ላይ ይገኛሉ የተባሉት እንግዶች በአጠቃላይ በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ብቻ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
አንዳንድ የዲያስፖራ አባላት ከዚህ ቀደም መሬትና የባንክ ብድር ይመቻችላሃል በሚል ቅስቀሳ ተታለው ወደሀገር ውስጥ በመግባት ከፍተኛ መዋዕለንዋያቸውን ያፈሰሱ ቢሆንም በቢሮክራሲው ችግሮች፣ በሙስናና ብልሹ አሰራር የከፋ ጉዳት ደርሶባቸው ለኪሳራ ጭምር ተዳርገው ወደመጡበት የተመለሱ ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዘጋቢያችን አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም በሀገሪቱ ምቹ ሁኔታ አለ በሚል የሚደረገው ቅስቀሳ ምን ያህል አሳማኝ ነው የሚለውን የዲያስፖራው አባላት ሳይመረምሩ እንዳይታለሉ መክረዋል፡፡