(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2011)የቦይንግ ኩባንያ በተከሰከሱት የኢንዶኔዢያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች አብራሪዎቹን ተጠያቂ አደረገ።
ከሶስት ሳምንት በፊት ኩባንያው በይፋ ሃላፊነቱን መውሰዱን ወደጎን በማድረግ አብራሪዎቹ የቦይንግን አውሮፕላኖች አጠቃቅም መስፈርት ባለሟሟላታቸው የተከሰተ አደጋ ነው ሲል አስታውቋል።
የሁለቱ አየርመንገዶች ባላስልጣናት ቦይንግ አቋሙን ቀይሮ አብራሪዎቹን ተጠያቂ ባደረገበት አስተያየት ላይ እስከአሁን ምላሽ አልሰጡም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የቦይንግ ኩባንያን እንቅስቃሴ በአንክሮ እየተከታተልን ነው ብለዋል።
ቦይንግ የተሰኘው የአሜሪካን የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ በኢንዶኔዢያና በኢትዮጵያ አየርመንገዶች ላይ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ ከሶስት ሳምንት በፊት የሰጠውን መግለጫ መቀልበሱን ነው ሲ ኤን ኤን የዘገበው።
የኩባንያው ዋና ሃላፊ ዴኒስ ሙይልበርግ ትላንት በሰጡት መግለጫ በሁለቱ አየርመንገዶች ንብረት በሆኑት ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖች ላይ የደረሰው አደጋ አብራሪዎቹ የተቀመጠውን የበረራ ስነስርዓት ደንብ ባለመከተላቸው ነው ብለዋል።
የማክስ 737 አውሮፕላኖች ሶፍትዌር ፍተሻ ተደርጎ በሚገባ መሰራታቸውንና ምንም ችግር እንደሌለባቸው አረጋግጠናል የሚሉት ዋና ሃላፊው ለአደጋው መንስዔ የሆነው ችግር እንዳይከሰት መደረግ ያለበትን የአሰራር ሂደት አብራሪዎቹ በአግባቡ አልተከተሉም ሲሉ ከሶስት ሳምንት በፊት የሰጡትን ማብራሪያ የሚቃረን አስተያየት አቅርበዋል።
ሃላፊው ዲኒስ ይቅርታ ጠይቀው ጥፋቱ የኩባንያቸው መሆኑን እንዲሁም የቀደመው መግለጫቸው የአደጋውን መንስዔ ችግሩን አውቀነዋል፣ሃላፊነቱን እንወስዳለን፣ እንዴት እንደሚስተካከልም እናውቅበታለን ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ቦይንግ በሁለቱ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ላይ በደረሰው የማክስ 737 አውሮፕላን አደጋ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል።
በመጋቢት 10 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ በኋላ የባለአክሲዮኖች ገበያው በ10 በመቶ ማሽቆልቆሉን መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚሁ አደጋ ምክንያት ትርፉ በ21 በመቶ መውረዱንም የሲ ኤን ኤን ዘገባ ያመለክታል።
ቦይንግ የገጠመውን ከፍተኛ የተቀባይነት ቀውስ ለመታደግ በዋና ሃላፊው ቀደም ተብሎ የተገለጸው መረጃ ኩባንያውን ክፉኛ እንደጎዳው ተገልጿል።
ኩባንያውን ለማትረፍ ሲባል የደረሱት አደጋዎች በኩባንያው ስህተት አለመሆኑን ራሳቸው እንዲያስተባብሉ መደረጉን ነው ታዛቢዎች የሚገልጹት።
ሁለቱም አውሮፕላኖች በተመሳሳይ የሶፍት ዌር ችግር ለአደጋ መዳረጋቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር የምርመራ ውጤቱን ይፋ ሲያደርግም ከአብራሪዎቹ ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልነበረ መግለጹ የሚታወስ ነው።
ቦይንግ ኩባንያ አዲስ ይዞ ስለመጣው አቋም በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።