የቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸውን ሊያፈርስ የሄደውን የፖሊስ ሀይል ተባብረው በመመከት ወደ መጣበት መለሱት

መስከረም ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በፖሊስና በነዋሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ፤”መብታችንን አናስነካም!”ባሉ ነዋሪዎች ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

የአስተዳደሩ ግብረ ኃይል  ባለፈው ሐሙስ በዶዘር በመታገዝ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ ያደረገው ሙከራ፤ በአካባቢው ነዋሪዎች ብርቱ ተቃውሞ ተቋርጧል፡፡

እንደ ሪፖርተር ዘገበ፤ በወቅቱ በነዋሪዎቹና በፖሊስ መካከል የጥይት ተኩስና የድንጋይ ውርወራ ተካሂዶ ነበር፡፡

ባንዲራ በማውለብለብ ባካሄዱት ተቃውሞ መኖሪያ ቤታቸውን ከመፍረስ የታገዱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግሥት እንዲያነጋግራቸው  ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በደረሰበት ከፍ ያለ ተቃውሞ ሳቢያም በፖሊስ የታጀበው አፍራሽ ግብረ ኃይል ሥራውን አቋርጦ ተመልሷል፡፡

እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጨረቃ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ አስተዳደርም ሆነ የከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር እነዚህ ግንባታዎች ሕገወጥ ናቸው በማለት ሦስት ጊዜ ቢያፈርሷቸውም፤ነዋሪዎቹ የፈረሱትን ቤቶች በድጋሚ በመገንባት ኑሮአቸውን ሲገፉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሳልፍ አህመዲን፦” መሬት ውስን ሀብት እንደመሆኑ በወረራ ሊያዝ አይገባም፡፡ ሕግን የማስከበሩ ተግባር የሚቀጥል በመሆኑ በቦሌ ቡልቡላ የተገነቡ የጨረቃ ቤቶችም ይፈርሳሉ”ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ግን፦” መንግስት ለዘለቄታው የሚሆነንን መጠለያ ሳይሰጠን ቤታችንን አናስፈርስም!” የሚል ጠንካራ አቋም ይዘዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide