የብጹፅ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዜና ረፍት የመላው ኢትዮጵያውያን መነጋገሪያ ሆኗል

ነሀሴ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዘጋቢዎቻችን እንደገለጡት የአቡነ ጳውሎስን ድንገተኛ ዜና እረፍት ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው ። አንዳንድ ሰዎች አቡኑ በዋልድባ እና በሌሎች ገዳማት ላይ ለፈጸሙት በደል እግዚአብሄርን አሳዝነዋል የሚል አስተያየት ሲሰጡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የሞታቸው መንስኤ ከአቶ መለስ ዜናዊ ደህንነትጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አባት አቡነ ጳውሎስ ለሞት የሚያበቃ በሽታ እንዳልነበረባቸው መስክረው፣ ምናልባትም እግዚአብሄር ሊሰራው ያሰበው አንድ ተአምር ሳይኖር አይቀርም ብለዋል።

ጳጳሱን ለመተካት ስድስት ጳጳሳት በዕጩነት ለመቅረብ ቅድሚያ እንዳላቸው ለቤተክርስቲያን ቅርብ የሆኑ ሰዎች እየተናገሩ ነው።

የሀይማኖት አባቶች እንደተናገሩት፤ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ቀኖና መሰረት፤ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት የሚመረጡት ብፁዕ አባት፤ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል መሆን አለበት።

በዚህም መሰረት ዛሬ በሓላፊነት ላይ የሚገኙትና በሦስተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1971 ዓ.ም የተሾሙት አባቶች፤ ከሀገር ውስጥ፡- ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ በውጭ ሀገር በሓላፊነት ላይ ከሚገኙት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፤ በስደት ከሚገኙትና የዕርቀ ሰላም ንግግር ከሚያካሂዱት ብፁዓን አባቶች መካከል ደግሞ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ናቸው።

በቤተ-ክርስቲያኗ ህግ መሰረት አቡነ-ጳውሎስ መተካት ያለባቸው፦ ከነዚህ ስድስት አባቶች መካከል በአንደኛቸው ነው።

ከዚህ አኳያ አዲሱ  የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ማን ይሆኑ?የሚለው ከወዲሁ የብዙዎችን ቀልብ ሰቅዞ መያዙና ብዙዎችን እያነጋገረ መሆኑ ታውቋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ የአቡነ ጳውሎስ የቀብር ሥነ ሥርዐት÷ ኀሙስ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም  በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲከናወን ወስኗል።

“ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጎን ይቀበራሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ   የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ-ጳውሎስን ዜና ዕረፍት ተከትሎ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ የሀዘን መግለጫ  በመንግስት ብዙሀን መገናኛዎች አለመሰማቱ፤በመዲናይቱ ነዋሪዎች ዘንድ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርፈዋል፤አለያም ምንም ነገር ማወቅ እስካይችሉ ድረስ ራሳቸውን ስተዋል የሚል እምነት እያሳደረ መምጣቱን የኢሳት ዘጋቢዎች አመልክተዋል።

የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስቴር ተብሎ ከተሰማ አጭር መግለጫ ባሻገር  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ዜናዊ በግላቸው ያተላለፉት የሀዘን መልዕክት አልተሰማም።

አቶ መለስ በግላቸው ለክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ እና ለሌሎች ሰዎች ያስተላለፏቸውን የሀዘን መልዕክቶች ያስታወሱት እነኚሁ ነዋሪዎች፤ አቡነ-ጳውሎስ ከተቀመጡበት ታላቅ የሹመት ቦታ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ -ከብጹዕነታቸው ጋር ያላቸው ቅርበት ከሌሎቹ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በፓትርያርኩ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ካለው የጠበቀ ቅርበትና ፍቅር አኳያ አቡነ-ጳውሎስ፦ አቶ መለስን የሚጠሩት ፦”ልጁ” እያሉ እንደሆነ ከቤተ-ክህነት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide