የብአዴን ወጣቶች ሊግ አባላት ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፈን ለመታገል እምነትም ጽናትም የለንም አሉ

ግንቦት ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ወጣቶቹ ይህን የተናገሩት በባህርዳር በመካሄድ ላይ ባለው የብአዴን ወጣቶች 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በክልሉ ካለው 20 ሚልዮን ህዝብ መካከል 429 ሺ 520 የሚሆኑ ወጣቶችን አባል አለኝ የሚለው ብአዴን ከአደገኛ ቦዘኔነት እስከ ልማት አርበኛ ስም የሚነግድበት ወጣት ከገዥው ፓርቲ ያተረፈው ኪሳራ መሆኑን ተሰብሳቢዎች በአስተያየት አመልከተዋል፡፡
ከመላው የክልሉ ወረዳዎች የተወጣጡ ከ3000 በላይ ወጣቶች በጥቃቅን እና አነሰተኛ የዘርፉ ስኬታማነት በሚል ርዕስ የቀረበውን ሪፖርት ካደመጡ በሁዋላ የአህአዴግ ንግድ ትርፉ ኪሳራ ነው ብለውታል፡፡
በጥቃቅን እና አነሰተኛ ፖሊሲ ስም ፍጹም ክህደት ተፈጸመብን የሚሉት ወጣቶች መማራችን የጠቀመን ነገር የለምም ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ከ97 በፊት የገጠመውን የስራ አጥነት የተቃውሞ ፈተና በአደገኛ ቦዘኔ ስም በእስራት ሊፈታ የሞከረ ሲሆን ያኔ በተቀሰቀሰው የለውጥ ማዕበል ችግሩ እንዲስተካከል ለማድረግ ሞክሩ ሳይሳካለት ቀርቷል
“በሃሰት እንድንኖር እየተገደድን ነው” ያሉት ወጣቶች ፣  ከኢህአዴግ ጎን ቁሞ ለመሰለፍ ተስፋችን ተሞዋጦ አልቋዋል  እምነትም የለንም ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ በ19 60 ዎቹ የነበሩትን የወጣቶች እንቅስቃሴ እንደነ ዋለልኝ እና ማርታ የመሳሰሉትን በማንሳት ሌላ ታሪክ ያሰፈልጋል ያሉም ነበሩ።

የግዳጅ  የድጋፍ ሰላማዊ  ሰልፍ እንዲሁም ትርፍ የሌለው የአዲስ ራዕይ መጽሄት ውይይት አሰልችና ጊዜ ጨራሺ ነው ያሉት ወጣቶች በመዋጮ ሰበብ የሚጠየቁት ክፍያ መብዛቱን፣  የሚናፍቁትን ስራ እንደላገኙና የቤተሰብ ሸክም ለመሆን ስርዓቱ እንዳሰገደዳቸው ተናግረዋል፡፡
ወጣቱ ቁርጠኛ አልሆነም ያሉት የሊጉ ለቀመንበር አቶ ስቡህ ገበያው በየደረጃው ያሉ አመራሮች የአድርባይነት እና የአቅም ክፍተት የወጣቱን ተጠቃሚነት ፈተና ውስጥ ከተውታል ብለዋል፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት፤ብልሹአሰራር ፤ሙስና በወረረው ዓመራር መሃል መታገል እና ለውጥ ማምጣት ትግሉን እንደ አዲስ ከመጀመር ይታሰባል ያሉት የወጣት አመራሮች ችግሩን ለመፍታት መታገል አለብን ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን የጠየቅነው አቶ ስቡህ ለኢሳት እንደገለጸው መድረኩ ፍጥጫ የበዛበት እንደነበር አምኖ፣ ወጣቶች ከኢህአዴግ ጎን አንቆምም ማለታቸውን ግን አስተባብሎአል። ( )

ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። እሳቸውም ” እናንተን ወጣቶች ይዘን የአውራ ፓርቲነታችንን እናረጋግጣለን “ብለዋል። ጉባኤውን ለማዘጋጀት 1 ሚሊዮን ብር መመደቡም ታውቋል።