(ኢሳት ምንጮች–መስከረም 12/2010)የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ያለስምምነት መበተኑን ምንጮች ገለጹ።
በስልጣን ላይ ለ2 አመታት የቆየው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ ምርጫ ማካሄድ ይጠበቅበት ነበር::የሚባረሩ እንዳሉም ይነገራል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በግጨው የስምምነት ጉዳይና በቅማንት ሕዝበ ውሳኔ ውጤት መነታረካቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ በስምምነት የተጠናቀቀ ለማስመሰል የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
አቶ ደመቀ ግን በአባላቱ የነበሩትን ልዩነቶችና ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ይፋ አላደረጉም።
ጥልቅ ተሀድሶው የታሰበለትን አላማ በተሟላ መንገድ እንዳላሳካ ግን ለመናገር ተገደዋል።
በተለይም የህዝብ ጥያቄዎችን የመመለስ ተግባር ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በከፊል መካሄዱን ነው የገለጹት።
በተለይም የግጭት መንስኤ የሆኑ የወልቃይትና የግጨው እንዲሁም የቅማንት ጉዳዮች ግን ለማእከላዊ ኮሚቴው መጨቃጨቅና ስምምነት ላይ አለመድረስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የወልቃይት ጉዳይ ሳይፈታ የግጨው ጉዳይ ለምን ቅድሚያ ተሰጠው፣የቅማንት ማንነት ጥያቄ ከብአዴን ይልቅ ከበስተኋላው የሚገፋው አካል አለ የሚሉት ጉዳዮች እንዳላግባቧቸው ታውቋል።
በማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ከባድ መካረርና ውዝግብ የፈጠረው ግን ከብአዴን ካድሬዎች እንዲታሰሩና ከግጭቶች ጋር በተያያዘ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተጠያቂ ይደርጋሉ በተባሉ ሰዎች ዙሪያ ልዩነት መፍጠራቸው ነው።
እንደ ምንጮች ገለጻ ግዛት አብየ፣ ደሴ አሰሜና አገኘሁ ተሻገር ከሰሜን ጎንደር ችግር ጋር በተያያዘ በተጠያቂነት እንዲታሰሩ በሕወሃት በኩል ፍላጎት አለ።
በአማራ ህዝባዊ አመጽ ጊዜ የልዩ ሃይል አዛዥ የነበሩ ግለሰብና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ ወርቁን ከስልጣን ለማንሳት በተደረገው ግምገማም ስምምነት አልተደረሰም ተብሏል።
እናም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለክልሉ ምክር ቤት በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ የተሟላ መግባባት እንደሌላቸው ነው የተገለጸው።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለክልሉ በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ የተሟላ መግባባት እንደሌላቸው ነው የተገለጸው።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የ2 አመት የስልጣን ጊዜው የተጠናቀቀ ቢሆንም ምርጫ አላካሄደም።
በመጪዎቹ ስብሰባዎች ግን ከስልጣን የሚወርዱና የሚወጡ የብአዴን ካድሬዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በግጨው ጉዳይ ላይ ሕወሃት በፈለገው መንገድ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ በሕዝብ ዘንድ በመጠላታቸው አሁን ቢወርዱ ችግር የለውም በሚል በሕወሃት ባለስልጣናት ዘንድ ምክክር እየተደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።