(ኢሳት ዜና–መስከረም 2/2010) የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከነገ በስቲያ ሲጀምር የግጨው ስምምነትን ተከትሎ ባለው ተቃውሞ ዙሪያ እንደሚመክር የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በሰሜን ጎንደር የቅማንት የሕዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት በአካባቢው ውጥረት መከሰቱም የማእከላዊ ኮሚቴው መነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።
ማእከላዊ ኮሚቴው በቀጣይ ጊዜ ከስልጣን በሚወገዱ አባላት ዙሪያም ይመክራል።
የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በሶስት ቡድን የተከፈለ በቅርበትና በአካባቢ ልጅነት የተደራጀ የስልጣን መሳሳብ ያለው እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
በአንድ ወገን የወሎ ተወላጆችና ለሕወሃት ቅርበት ያላቸው እነ አቶ አለምነህ መኮንን በሌላ ወገን በጸረ ሰላም አካባቢ ከሚፈረጀው ጎንደር የመጡና ለአማራ ሕዝብ የሚቆረቆሩ ተደርገው የሚታሰቡ ናቸው።
በአዲስ አበባ ፌደራል መንግስት ስልጣን ላይ ያሉና መሃል ሰፋሪዎች እንዳሉም ይነገራል።
በዚህ ሶስት ምድብ የተከፈለው የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ታዲያ ከነገ በስቲያ ጀምሮ ማለትም ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 8/2010 ድረስ መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ ምንጮች ገልጸዋል።
የስብሰባው ዋና አጀንዳም በክልሉ በተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ አፈጻጸምና ከዚህ ጋር ተያይዞም የትግራይና የአማራ ክልሎችን በሚያወዛግቡ የግጨው ስምምነትና የቅማንት ሕዝበ ውሳኔ ጉዳይ ላይ ይመክራል ተብሏል።
የአማራ ክልል ግጨውና ጎቤን ለትግራይ ክልል አሳልፎ በመስጠቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳል የሚል ስጋት መኖሩ ይነገራል።
የቅማንትን ሕዝበ ውሳኔ በመቃወም የአካባቢው ሕብረተሰብ ከታጣቂዎች ጋር መጋጨት መጀመሩ ብአዴንን እንዳሳሰበው ምንጮች ይናገራሉ።
ሕብረተሰቡ የወልቃይት ችግር ሳይፈታ ስለቅማንት መተኮሩ ምን የተሸረበ ጉዳይ ቢኖር ነው በሚል መወያየት ላይ መሆኑ ነው የሚነገረው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የብእዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በጸረ ሰላም ሀይሎች አመለካከት ተውጣችኋል የተባሉ አመራሮችን ከስልጣን ለማስወገድ እንደሚመክርም ታውቋል።
በሰሜን ጎንደር ያለውን ከፍተኛ አመራር ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር እቅድ መኖሩንም ምንጮች ገልጸዋል።
ብአዴን ማንን አባሮ ማንን ሊያስቀር እንደሆነ ባይታወቅም በካቢኔው ውስጥ ሽግሽግና ድልድል በሚል የስልጣን ሹም ሽር ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።