የብሪታንያ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰራጩ የሙዚቃና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ያጸደቀው 5 ሚሊዮን ፖውንድ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት (ታህሳስ 10 ፥ 2009)

የብሪታንያ መንግስት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተቋማት ለሚካሄዱ/ለሚሰራጩ የሙዚቃና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ድጋፍ ያጸደቀው 5 ሚሊዮን ፖውንድ በሃገሪቱ ባለስልጣናት ዘንድ ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

የሃገሪቱ መንግስት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ “የኛ” በሚሰኙ አባላት ዘንድ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱ ናቸው በማለት ከጥቂት አመታት በፊት ድጋፍ መስጠት መጀመሩን ዴይሊ ሜይል የተሰኘ የብሪታኒያ ጋዜጣ ዘግቧል።

ይህንኑ የሙዚቃና ድራማዊ ፕሮግራሞ ለቀጣዩ ሁለት አመታት ለመደገፍ የብሪታኒያ መንግስት የ5.2 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ100 ሚሊዮን ብር) በላይ ድጋፍ ማጽደቁን አስታውቋል።

የገንዘቡ ይፋ መደረግን ተከትሎ በርካታ የብሪታኒያ ባለስጣናት ለኢትዮጵያ የተለገሰው ገንዘብ ለሌላ አላማ ሊውል ይችላል በማለት ድርጊቱን መቃወም እንደጀመሩ ጋዜጣው ሰኞ ለንባብ ባበቃው እትሙ አስነብቧል።

ተቃውሞን ማቅረብ የጀመሩ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከታክስ ከፋይ ብሪታኒያዊያን የተሰበሰበው ገንዘብ ለታሰበው አላማ ከመዋሉ ውጭ ገንዘቡን እንደማባከን ይቆጠራል ሲሉ ተቃውሞን በማቅረብ ላይ እንደሆኑ ታውቋል።

ከሶስት አመት በፊት “የኛ” የተሰኘውን የሙዚቃና ድራማዊ ስራ ለመደገፍ የብሪታኒያ መንግስት አራት ሚሊዮን ፓውን ስተርሊንግ (ከ100 ሚሊዮን ብር) በላይ ሰጥቶ እንደነበር ጋዜጥእው በምርመራ ጋዜጠኝነት ባካሄደው ተልዕልኮ ማወቅ እንደተቻለ አውስቷል።

በወቅቱ ተመሳሳይ ቅሬታን አቅርበው የነበሩ የተለያዩ አካላት የገንዘብ ድጋፍ “የኛ”ን ለመደገፍ ለ154 አመት ይበቃል ሲሉ ተቃውሞን አሰምተው እንደነበር ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል።

የብሪታኒያ መንግስት ለዚህ ፕሮግራም ድጋፍ ሲሰጥ የቆየውን ገንዘብ ለህዝብ ይፋ አድርጎት እንደሚያውቅ ያስታወቀው ጋዜጣው አዲሱ የገንዘብ ድጋፍ በብሪታኒያ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ድረገፅ ላይ መስፋፋትን አክሎ ገልጿል።

በርካታ የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሃገሪቱ ዜጋዋ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለማስፈታት ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዘርፍ ብዙ ድጋፎች እንድታቋርጥ ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ማንኛውም ድጋፍ ላይ ተቃውሞን እያሰሙ የሚገኙ ባለስልጣናት ገንዘቡ ከታለመለት አላማ ውጭ ይውላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ይገልጻል። ሃገሪቱ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የትምህርትና ጤና ድጋፍ ተመሳሳይ አለም አቀፍ ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቶ ብሪታኒያ በአለም ባንክ በኩል ለዘርፉ የምትሰጠው ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጓም የሚታወቅ ነው።

የብሪታኒያ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ተቋም በየአመቱ ለትምህርትና ጤና ድጋፍ ሲሰጥ የነበረው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ በጋምቤላና ሌሎች አካባቢዎች ሲካሄዱ ለቆዩ የመሬት ቅርምት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ መዋሉን አለም ባንክ የተቋቋመ ገለልተኛ ቡድን ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ሃገሪቱ ለዘርፉ የምትሰጠውን ድጋፍ ያቋረጠች ሲሆን፣  የአለም ባንክ በበኩሉ ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን እንዲወሰድ በወቅቱ ይፋ አድርጓል።