የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የጸጥታና የደህንነት ድጋፍ እንዲቆም ጠየቁ

ኢሳት (መጋቢት 12 ፥ 2008)

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ተከትሎ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የጸጥታና የደህንነት ድጋፍ እንዲቆም አሳሰቡ።

ሃገሪቱ ዜጋዋ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው በእስር ላይ እያሉ በየአመቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለጸጥታና ደህንነት ስልጠናዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗን ጋዜጣው የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ባቀረበው ዘገባ አስፍሯል።

ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ይኸው ድጋፍ በሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩልና በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ አዲሱን ፕሮግራም ባለፈው አመት መጀመሩም ታውቋል።

የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ቢያረጋግጥም ዝርዝር መረጃን ከመስጠት መቆጠቡን ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

ይሁንና፣ የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ብሪታኒያ የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቋርጥ የሚጠይቅ ዘመቻ መክፈታቸውን ከጋዜጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

ሪፕሪቭ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ብሪታኒያ ቀጥላ ያለው ድጋፍ አሳሳቢ የሆነ ጥያቄ አስነስቶ እንደሚገኝ ገልጿል።

የስቃይ ሰለባ በሆኑ ሰዎች ዙሪያ የሚሰራው የሬድሬስ  የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የህግ አማካሪ የሆኑት ኬቪን ላኡ በበኩላቸው ብሪታኒያ የአቶ አንዳርጋቸው መፈታትን ከማሳሰቧ ይልቅ ለኢትዮጵያ የጸጥታ አገልግሎት ድጋፍ መቀጠሏ ፍትሃዊ አለመሆኑን ለኢንዲፔንደንት ጋዜጣ አስታውቀዋል።

የፓርላማ አባላትም በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለሚያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ደብዳቤን በመጻፍ አቶ አንዳርጋቸው ያለምንም ቅደመ-ሁኔታ እንዲፈቱ ግፊትን እንዲያደርጉ ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል።

ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙት ካሜሮን በሁለቱ ሃገራት መካከል ያሉ የጸጥታና የደህንነት ትብብሮችን በማንሳት ሰፊ ውይይትን እንደሚያካሄዱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይም በሁለቱ ወገኖች መካከል አጀንዳ ሆኖ እንደሚነሳም ይጠበቃል።