የብሪታኒያ ኩባንያ በአፋር ክልል ወርቅ ለማውጣት የደረሰው ስምምነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተጓትቶብኛል አለ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2009)

መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ የማዕድን ኩባንያ በአፋር ክልል ወርቅን ለማውጣት የደረሰው ስምምነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መጓተቱን ማክሰኞ ገለጸ።

ከፊ ሚነራል የተባለው ይኸው ኩባንያ፣ ባለፈው አመት የወርቅ ቁፋሮን በክልሉ የቱሉ ካፒ ፕሮጄክት ለመጀመር ከመንግስት ጋር ስምምነት የደረሰ ሲሆን፣ ፕሮጄክቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት እንደሚፈልግ ከኩባንያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ይሁንና ኩባንያው ስራውን ለመጀመር የያዘው እቅድ በጥቅምት ወር ተግባራዊ በተደረገው የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ ሊስተጓጎል መቻሉን የአክሲዮን ድርሻ አባላቱ ባሰራጨው መልዕክት አስታውቋል።

ኩባንያው ወደ ስራ ባለመግባቱ ምክንያት ከባለሃብቶች ሊሰበሰብ የታቀደ ገንዘብ ያልተገኘ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ወደ ኢንቨስትመንቱ መግባት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ውሳኔያቸውን በድጋሚ ያጤኑታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የአለም ባንክ ሲገልፅ ቆይቷል።

መንግስት በበኩሉ አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት በመኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአራት ወር እንዲራዘም መወሰኑ የሚታወስ ነው። ይሁንና የአዋጁ መራዘም በቱሪዝም ዘርፉ እንዲሁም በሃገሪቱ ኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን እንደሚቀጥል የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ኩባንያ ከመንግስት ጋር የደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በተያዘው የፈረንጆች አመት መግቢያ ላይ ስራውን ለመጀመር እቅድ ይዞ እንደነበር በድረ-ገጹ አስነብቧል።

ኩባንያው ፕሮጄክቱ መስተጓጎሉን ቢገልፅም መቼ ወደስራ እንደሚገባ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የድርጅቱ የአክሲዮን አባላት ፍላጎታቸው ወጥ ሊሆን አለመቻሉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚሁ የወርቅ ፕሮጄክት 20 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ለመረዳት ተችሏል።