ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)
የብሪታኒያ አለም አቀፍ ማሰረጫ ጣቢያ (BBC) ሶስት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ጨምሮ በ11 የተለያዩ ሃገራት ቋንቋዎች በፈረንጆች አዲስ አመት የራዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎት እንደሚጀመር ይፋ አደረገ።
የማሰራጫ ጣቢያው ከአንድ አመት በፊት አገልግሎቱን ለመጀመር ይረዳው ዘንድ እቅዱን ለብሪታኒያ መንግስት አቅርቦ በጀትን በመጠባበቅ ላይ እንደነበር ይታወሳል።
ለቀረበው ጥያቄ ይሁንታ ያገኘው የብሪታኒያ አለም አቀፍ የማሰራጫ ጣቢያ በጥቂት ወራት ውስጥ በኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ትግሪኛ እንዲሁም በሌሎች ስምንት ቋንቋዎች አዲስ ስርጭት ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን የጣቢያው ሃላፊ ቶኒ ሃል ረቡዕ አስታውቀዋል።
የማሰራጫ ጣቢያው በ11 ቋንቋዎች በአዲስ መልክ ለመጀመር የያዘው የስርጭት አገልግሎት በቢቢሲ ታሪክ በ70 አመት ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያውና መጠነ ሰፊ መሆኑን የዜና አውታሩ ዘግቧል።
የማሰራጫ ጣቢያው ከአንድ አመት በፊት እቅዱን ይፋ ባደረገ ጊዜ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ቅሬታዎች በተደጋጋሚ የሚቀርብባቸው ሃገራት በአዲሱ ፕሮግራም የቅድሚያ እድል እንደሚሰጣቸው ገልጾ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ ሩሲያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ በሰብዓዊ መብት መከበር ችግሮች የሚታይባቸው በመሆኑ ዋነኛ ትኩረት መሆናቸውን የማሰራጫ ጣቢያ ሃላፊዎች በወቅቱ ይፋ ማድረጋቸውም አይዘነጋም።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ጣቢያው ኢትዮጵያን በዚህ መልኩ መፈረጁ ተገቢ አይደለም በማለት ቅሬታን አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ የማሰራጫ ጣቢያው በሶስቱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስርጭት ለመጀመር መወሰኑ በሃገሪቱ ያለውን የመረጃ ክፍተት እንደሚያወግዝ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
“ይህንን ግዙፍ እና በአይነቱ ልዩ የሆነውን የማስፋፊያ ስርጭት ይፋ መደረግ ስናበስር ደስታችን የላቀ ነው” ሲሉ የገለጹት የጣቢያው ሃላፊ ቶኒ ሃል፣ ውሳኔው ለጣቢያው ታሪካዊ ዕለት ተደርጎ እንደሚታይ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የማሰራጫ ጣቢያው በቅርቡ የሚጀምረው ይኸው አዲስ ስርጭት ወቅታዊ መረጃዎችን የማህበራዊ ድረገጾችን ጨምሮ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ የሚያደርግ መሆኑን ታውቋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ዙሪያ የሚሰራጨው አገልግሎት 30 ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በአጭርና በመካከለኛ ሞገድ የሚተላለፉ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ያቀፈ እንደሆነ የጣቢያው ሃላፊዎች የአገልግሎት መጀመር አስመልክቶ ለአለም አቀፉ መገናኛ ተቋማት በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ አመልክተዋል።
የብሪታኒያ የማሰራጫ ጣቢያ በቅርቡ በ11 ቋንቋዎች የሚጀምረው አዲስ የስርጭት አገልግሎት የቋንቋ ብዛቱን ወደ 40 የሚያደርሰው ሲሆን፣ ጣቢያው በቀጣዮቹ ስድስት አመታት ውስጥ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን በአገልግሎቱ ሽፋን ለማዳረስ እቅድን ይዟል።
የብሪታኒያ መንግስት ጣቢያው ለሚጀምረው አዲስ አገግሎት በአንድ አመት 85 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ በጀት ማፅደቁንም ለመረዳት ተችሏል።