የብሪታኒያ መንግስት ዜጎቹ ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚያደርጉት ጉዞ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠየቀ

ኢሳት (መስከረም 25 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል በአዲስ መልክ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ዜጎቹ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ ረቡዕ በድጋሚ አሳሰበ።

ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ/ደብረዘይት ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ያወሳው የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በምስራቅ አርሲ ዞን ስር በምገኙ የሻሸመኔ፣ መቂ፣ እንዲሁም የአምቦ ነቀምቴ፣ ሃዋሳ ከተሞች ተቃውሞዎች መቀስቀሳቸውን የብሪታኒያ መንግስት ለዜጎቹ ባሰራጨው የጉዞ ማሳሰቢያ አመልክቷል።

ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ የብሪታኒያ ዜጎች ወደ አማራ ክልል በሚያደርጉት ማንኛውም ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ያሳሰበ ሲሆን፣ ተቃውሞዎች በማንኛውም ሰኦት ወደ ሁከት ሊለወጡ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ወደ 20ሺ የሚጠጉ ብሪታኒያውያን እንደሚኖሩ የገለጸው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ዜጎች ከማንኛውም ህዝባዊ ስብሰባዎችና የተቃውሞ ትዕይንቶች ራሳቸውን እንዲያርቁ ባሰራጨው መልዕክት አሳስቧል።

ማክሰኞ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ለአንዲት አሜሪካዊ ሞት ምክንያት መሆኑን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የአሜሪካዊቷ ግድያን በማስመልከት ረቡዕ መግለጫ ማውጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ዕርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ሲካሄድ በነበረው ተቃውሞ አሜሪካዊቷ ይዞ ይጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ድንጋይ ሲወረውሩ በነበሩ ሰልፈኞች ጥቃት እንደተፈጸመበት የዜና አውታሩ በዘገባው አመልክቷል።

አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠበ ሱሆን ለዜጎቹ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲያደርጉ አሳስቧል።