የብሪታኒያ መንግስት በሰሜን ጎንዳር አካባቢዎች ያወጣው የጉዞ ጥንቃቄ ቀጣይ እንዲሆን ወሰነ

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

በቅርቡ በሰሜን ጎንዳር አካባቢዎች በመንግስትና በአርበኞች ግንቦት ሰባት መካከል ሲካሄድ የቆየ ውጊያ ተከትሎ የጉዞ ማሳሰቢያን አውጥቶ የነበረው የብሪታኒያ መንግስት ማሳሰቢያው ቀጣይ እንዲሆን ሰኞ በድጋሚ ወሰነ።

ለሃገሪቱ ዜጎች ማሳሰቢያን ያሰራጨው የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጸገዴ፣ በምዕራብና ታች አርማጭሆ የሰሜን ጎንደር ስፍራዎች አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ በመግለጫው አመልክቷል።

ከብሪታኒያ መንግስት በተጨማሪ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ በድጋሚ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ለሁለተኛ ጊዜ ማሳሰቢያውን ያሰራጨው የአሜሪካ መንግስት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ የደህንነት ስጋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ አሜሪካ እየሰጠች ያለችው ማሳሰቢያ በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ አይደለም በማለት ቅሬታውን በድጋሚ አቅርቧል።