ኢሳት (መጋቢት 4 ፥ 2009)
የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያና ሁለት የአፍሪካ ሃገራት ለአማራጭ የሃይል አቅርቦት ፕሮጄክቶች ሲሰጥ የቆየው በመቶ ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ “ብክነት” አስከትሏል የሚል ጥያቄን አስነሳ።
ሃገሪቱ ለዚሁ ፕሮጄክት ከስምንት አመት በፊት ወደ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ ገንዘብ ብትመድብም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እንዲሁም በማሊ የሃይል አማራጭን ተግባራዊ ለማደረግ የተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ታይቶባቸዋል የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ቴሌግራፍ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ያካሄደውን የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲሁም ቅሬታ አቅራቢዎችን ዋቢ በማድረግ ሰፊ ዘገባን አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ከንፋስ የሃይል ማመንጫን ለማግኘት እንዲሁም በኬንያና ማሊ የጸሃይና ከቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሃይልን አገልግሎት ላይ ለማዋል ሲሰጡ የነበሩ የገንዘብ ድጋፎች ዋነኛ ጥያቄ ማስነሳታቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።
ለአንድ ፕሮጄክት ተመድቦ የነበረ ወደ 260 ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ ለ100 ብቻ የብሪታኒያ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ሃይል ማመንጨቱን ጋዜጣው በዚሁ ዘገባው አስፍሯል።
ይኸው ድጋፍ በተለያዩ አካላት ዘንድ ጭምር ጥያቄ አስነስቶ እንደሚገኝ ያስታወቀው ቴሌግራፍ ጋዜጣ፣ የብሪታኒያ መንግስት ለአለም አቀፍ ድጋፍ እያዋለ ያለው ገንዘብ ተቃውሞን እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጿል።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት ብሪታኒያ ለዘርፉ እየሰጠች ያለው ድጋፍ በፕሮጄክቶቹ ማጠቃለያ ከስድስት አመት በኋላ የሚታይ ጉዳይ ነው ቢሉም የብሪታኒያው አለም አቀፍ የልማት ትብብር ፕሮጄቶቹ ላይ ስጋቱን እየገለጸ እንደሚገኝ ቴሌግራፍ ጋዜጣ አቅርቧል። ከአካባቢው ለውጥና ከአማራጭ የሃይል አቅርቦቶች ጋር የተያያዙ ፕሮጄክቶች ከፍተኛ ቸልተኝነት እና የገንዘብ ብክነት የታየባቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ዶ/ር ጆን ኮንስታብል ለጋዜጣው አስረድተዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የልማት ትብብሩ ሚኒስትሮች ለዘርፉ በመስጠት ላይ ያለው ድጋፍ ለሰብዓዊ ስራ ቢውል የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ለቴሌግራፍ ተናግረዋል።
በአለም ባንክ ተቆጣጣሪነት ተግባራዊ እየተደረገ ላለው ለዚሁ ፕሮጄክት ወደ 6.7 ቢሊዮን ፓውን ገንዘብ የተመደበ ሲሆን፣ ብሪታኒያ ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ አንድ ሶስተኛውን እንደምትሸፍን ለመረዳት ተችሏል።
ይኸው ፕሮግራም ኢትዮጵያን ጨምሮ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉ 28 ሃገራትን በሃይል አቅርቦት ለማገዝ ያለመ ቢሆንም፣ ፕሮጄክቱ የተጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላስገኝ ተመልክቷል።
በሆንዱራስ ያሉ ሁለት እንዲሁም በኔፓል የሚገኝ አንድ ፕሮጄክት ብቻ የአረንጓዴ የኤሌክትሪክ ሃይልን ማመንጨት የጀመሩ ሲሆን፣ ድጋፍ የተደረገላቸውን 20 ፕሮጄክቶች ያስገኙት በጎ ውጤት አለመኖሩን ጋዜጣው በሰፊው ዘገባው አካቷል።
እነዚሁ ፕሮጄክቶችን እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 በሰዓት 2ሺ 600 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ድረስ 276 ሜጋዋት ብቻ ማመንጨታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት ባለፉት ስድስት አመታት ከተያዘላቸው እቅድ ውስጥ 1 በመቶውን ብቻ ማሳካት እንደቻሉ ቴሌግራፍ ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
የብሪታኒያ የፓርላማ አባልና የአለም አቀፍ ልማት ኮሚቴ አባል የሆኑት ኒጎል ኤቫንስ በበኩላቸው ሁኔታው እጅ አስደንጋጭ መሆኑንና ብሪታኒያ እየሰጠችው ባለው የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ጥያቄ ማስነሳቱን ገልጸዋል።
የአለም ባንክ በበኩሉ ፕሮጄክቶቹ ሲጠናቀቁ ውጤታቸው እንደሚታወቅና ጊዜውን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ለዘገባው በሰጠው ምላሹ አስታውቋል።
የብሪታኒያ የፓርላማ አባላትና የመገናኛ ብዙሃን በቅርቡ ሃገሪቱ ለኢትዮጵያ ለሴቶች የማህበረሰብ ትምህርታዊ ድጋፍ ስትሰጥ የቆየችው ድጋፍ ውጤትን አላመጣም የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ የ5.5 ሚሊዮን ፓውንድ ልገሳ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
ይኸው “የኛ” በሚል የሙዚቃ ቡድን አባላት ይካሄድ የነበረው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ የሚተላለፉ ትምህርታዊ ሙዚቃዎችን እንዲሁም ድራማዎችን ለህዝብ ሲያቀርብ ቆይቷል።