የብሪታኒያ መንግስት ለትምህርታዊ ፕሮግራሞች ሊሰጥ የነበረው የ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደገና እንዲታጤን መወሰኑ ተገለጸ

 

ኢሳት (ታህሳስ 11 ፥ 2009)

የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስር ባሉ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለሚተላለፉ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ሊሰጥ የነበረው የ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደገና እንዲታይና እንዲጠና ወሰነ።

የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የተወሰነው የ5.2 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ ድጋፍ ከታለመለት አላማ ውጭ ሊውል ይችላል ሲሉ ሰኞ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ዴይሊ ሜይል ጋዜጣን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

በተለያዩ ባለስልጣናት የቀረበውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ማብራሪያን ለመስጠት የተገደዱት የብሪታኒያ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ሃላፊ  ፕሪቲ ፓቴል ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የተወሰነው ድጋፍ እንደገና እንዲጤን ይደረጋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ለሃገሪቱ የፓርላማ አባላት ምላሽ የሰጡት ሃላፊዋ ከታክስ ከፋዮች የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት አላማ እንዲውል ግልጽ የሆነ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማረጋገጫን ሰጥተዋል።

የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ እየሰጠ ያለው ድጋፍ ከታለመለት አላማ ውጭ እየዋለ ነው በማለት ቅሬታን የሚያቀርቡ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞ እያሰሙ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የሃገሪቱ መንግስት በሬዲዮና ቴሌቪዥን “የኛ” በሚል መጠሪያ በኢትዮጵያ ለሚተላለፉ የሙዚቃና ድራማ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ለቀጣዩ ሁለት አመታት ድጋፍ ለማድረግ 5.2 ሚሊዮን ፓውንድ ለመስጠት መወሰኑ ይታወቃል።

ይሁንና ድጋፉ ከታለመለት አላማ ውጭ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው የብሪታኒያ የፓርላማ አባላትና የተለያዩ አካላት የሃገራቸው መንግስት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን እንዲወስድ እየጠየቁ ይገኛል።

የብሪታኒያ መንግስት በሙዚቃና ድራማዊ ፕሮግራሞች ለሴቶች መብት መከበር ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የግለሰብ መብቶች እና በሀገሪቱ የሚከሰቱ ሁከቶች ችላ የማይባሉ ጉዳዮች መሆናቸውንም የሃገሪቱ የአለም አቀፍ የልማት ትብብር ሃላፊዋ ፓቴል ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

ከአንድ አመት በፊት የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ ሲሰጥ የነበረው የጤና እና የትምህርት ድጋፍ ለሌላ ትግባር ውሏል የሚል ተመሳሳይ ተቃውሞ ቀርቦበት እንደነበር ይታወሳል።

ይህንኑም ተከትሎ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረው የአለም ባንክ፣ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት አድርጎ ድጋፉ በጋምቤላ ክልል ሲካሄድ ለነበረ የመሬት ቅርምት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እንደዋለ መረጋገጡ ይታወቃል።

የምርመራ ውጤቱን ተከትሎም የብሪታኒያ መንግስት ለዘርፉ ሲሰጥ የቆየው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰኑ ኣይዘነጋም።