የብረታ ብረትና ኢንጂነሪን ኮርፖሬሽን ለአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡሶችን ለማቅረብ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ኮንትራት ተረከበ

ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2009)

የመንግስት የልማት ፕሮጄክቶችን ያለ ግልጽ ጨረታ በመረከብ ላይ የሚገኘው የብረታ ብረትትና ኢንጂነሪን  ኮርፖሬሽን ለአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡሶችን ለማቅረብ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ኮንትራት ተረከበ።

የህወሃት ጄኔራሎች የሚመሩት ኮርፖሬሽኑ 750 አውቶቡሶችን ለማቅረብ ከከተማው አስተዳደር ጋር የኮንትራት ስምምነት መድረሱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። የአዲስ አበባ መንገዶችና ትራንስፖርት ቢሮ በቀጣዩ ሳምንት ከኮርፖሬሽኑ ጋር የ3.5 ቢሊዮን ብር ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአውቶቡሶቹን ግብዓት ከቻይና በማስመጣት ደብረ ዘይት ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካው አውቶቡሶቹን በመገጣጠም ለከተማ አስተዳደር እንደሚያስረክብ ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና ቢሾፍቱ በመባል የሚታወቁት የከተማ አውቶቡሶች መለዋወጫን ጨምሮ የቴክኒክ ችግር እንዳለባቸው የተለያዩ አካላት ሲገልፁ መቆየታቸውን ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

በዚሁ ችግር የተነሳ አንበሳ አውቶቡስ ለአገልግሎት የሚያስቸግራቸው የአውቶቡስ ቁጥሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ በመሄድ ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

አንበሳ አውቶቡስ በአሁኑ ሰዓት 420 አውቶቡሶችን በስራ ላይ አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን ቁጥሩ ባለፈው አመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ24 በመቶ መቀነሱም የጋዜጣው ዘግባ አስፍሯል።

ቢሾፍቱ በመባል የሚታወቁትን የከተማ አውቶቡሶች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከአምስት አመት በፊት ጀምሮ በመገጣጠም ለመንግስት ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮጄክት ኮርፖሬሽኑ በ10 ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ገቢ ማግኘቱን ለመረዳት ተችሏል።

የህወሃት ንብረት የሆነው ኮርፖሬሽኑ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኮንትራት ሲረከብ መቆየቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁንና የስኳር ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ወደስራ ባለመግባታቸው ምክንያት መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጨምሮ ከ40 በላይ ኩባንያዎችን እያስተዳደረ የሚገኘው ኤፈርት አጠቃላይ ሃብቱ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት መረጃዎች ያመለክታሉ።