የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ ይረዳሉ በሚል በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተገጣጥመው ወደስራ ከተሰማሩ አውቶቡሶች የቴክኒክ አቁዋማቸው ብቃት መጉዋደልና የመለዋወጫ እጦት ጋር በተያያዘ በየቦታው በብልሽት በመቆማቸው ምክንያት የአዲስአበባ ከተማ የትራንስፖርት እጥረት እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ከአዲስአበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት በኮርፖሬሽኑ ከተገጣጠሙ 500 ገደማ የከተማ አውቶቡሶች ከ110 በላይ የሚሆኑት በብልሽት ምክንያት ከመስመር ውጪ ሲሆኑ የተቀሩትም በትንንሽ የቴክኒክ ችግሮች በየመንገዱ የሚቆሙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከተማዋ የትራንስፖርት እጥረት እንዲባባስ አንድ ምክነያት ሆኗዋል፡፡
አውቶቡሶቹ በአገር ውስጥ ሲገጣጠሙ ታሳቢ ተደርጎ ነበረው በብልሽት ወቅት የመለዋወጫ አቅርቦት በቅርብ ማግኘት ያስችላል በሚል እንደነበር ነገር ግን አምራቹ የብረታብረት ኮርፖሬሽን የመለዋወጫ ክምችት መያዝ ባለመቻሉ ተሽከርካሪዎቹ በቀላል ብልሽት ጭምር ሊቆሙ እንደተገደዱ ታውቆአል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የቢሮው ሠራተኞች እንደተናገሩት ይህ የመለዋወጫ አንገብጋቢ ችግር ሳይፈታና የቆሙ ተሸከርካሪዎች ማንሳት ሳይቻል ተጨማሪ ከ50 በላይ አውቶቡሶችን ኮርፖሬሽኑ እንዲገጣጥም መታዘዙ በአገር ሐብት ላይ መቀለድ ነው ሲሉ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል፡፡
አውቶቡሶቹ ቴክኒካዊ አቋማቸው ደካማ በመሆኑ ለአንበሳ አውቶቡስ ግልጋሎት ለማዋል አስቸጋሪ መሆኑን በተግባር መታየቱን የትራንስፖርት ቢሮው አንዳንድ ሰራተኞች ተናግረው በዚህ ጉዳይ ላይ ገንቢ አስተያየት መስጠት በራሱ በፖለቲካ የሚያስፈርጅና ልማትን እንደማደናቀፍ እያስቆጠረ በመሆኑ ብዙሃኑ ባለሙያ ጭምር ዝምታን መርጦአል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞችን በመያዝ ወደአማራ ክልል ለስብሰባ ሲጉዋዝ የነበረ በኮርፖሬሽኑ የተገጣጠመ አውቶቡስ አባይ በረሃ ላይ በመገልበጥ በርካታ ሰዎች ለሞት መዳረጉን መነገሩ ይታወሳል