(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2011)በቅርቡ በኢትዮጵያ የተቋቋመው የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከመድሎ በጸዳ መልኩ ስራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ዕምነታቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር የተነጋገሩት ዶክተር አብይ አህመድ ይህ በመቶ ዓመት አንዴ የሚገኝ አጋጣሚ ሃገርን ከማቀራረብና ሰላምን ከማምጣት አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ በተካሄደው በዚህ መድረክ የዕርቅ ኮሚሽን አባላትን መንግስት ከመደገፍ ውጭ ጣልቃ እንደማይገባባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አረጋግጠዋል።
41 አባላት ላሉት ለዚህ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስን በሰብሳቢነት የሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድ የህግ ባለሙያዋን የትነበርሽ ንጉሴን በምክትል ሰብሳቢነት መርጠዋል።
የኮሚሽኑ አባል የሆኑት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የኮሚሽኑን ሃላፊዎች እንዲያግዙ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኮሚሽኑ አባላት ለሌሎች ሃገራት ጭምር የሚተርፉ ተምሳሌታዊ ተግባር እንዲከውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን በአጼ ሃይለስላሴ መንግስት የትግራይ ገዢ የነበሩትን ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን ጨምሮ እስከ ኢህአዴግ ዘመን ያሉ የቀድሞ ባለስልጣናትን እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎችን ያካተተ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ዛሬ በይፋ ስራ መጀመራቸው ተገልጿል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ከቀትር በኋላ የተወያዩት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት በይፋ ስራ መጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።