(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት በአዲስ መልክ እየተዋቀረ መሆኑ ተነገረ።
በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት አሁንም ሕወሃቶች የተለያዩ መምሪያዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የውስጥ ደህንነት የነበረው መምሪያ በ3 ተከፍሎ አዲስ ተሿሚዎች መመደባቸው ተነግሯል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተለያዩ መምሪያዎች የተዋቀረ መሆኑ ይታወቃል።
ከነዚሁ መምሪያዎች መካከል በዋናነት የሚታወቀው የውስጥ ደህንነት ዋና መምሪያ ከ3 እንዲከፈል መደረጉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
እነዚሁም የክልሎች ዋና መምሪያ፣የጸረ ሽብርና የጸረ ስለላ ዋና መምሪያ እንዲሁም የኢኮኖሚና መልካም አስተዳደር የሚባሉ ናቸው።
በዚሁም መሰረት የጸረ ሽብርና የጸረ ስለላ መመሪያ ዳይሬክተር ሆኖ እንዲመራ የሕወሃቱ አማኑኤል ሲመደብ፣በክልሎች ዋና መመሪያ ዳይሬክተርነት ደግሞ ግርማ የተባለ ሰው መሾሙ ታውቋል።
ይህም የሰሜን ሸዋ ሰው ነው ተብሏል።
የኢኮኖሚና የመልካም አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርነቱን ደግሞ ደርበው የተባለ የጎጃም ሰው ይዛታል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል የጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተርነት ቦታን ይዞ የነበረው ወዲ ኮበል የተባለው ሰው ተነስቶ ምክትሉ ተሾመ የሚባል ግለሰብ መተካቱ ተሰምቷል።
ይህ ሰው የወሎ ሰው ሲሆን ሌሎች መምሪያዎች በሙሉ ግን በሕወሃት ሰዎች ተይዘዋል ተብለዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በዚህ ሰሞን በአባላት መለየትና በማሸጋሸግ ርምጃ ተጠምዷል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ በሙስናና በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው ቢባልም እስካሁን ግን ከቦታቸው አልተነሱም።
አቶ ጌታቸው አሰፋ በሃገሪቱ ውስጥ ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆናቸው ይነገራል።
በኢታማዦር ሹሙ በጄኔራል ሳሞራ የኑስ በጥሩ የማይነሱት አቶ ጌታቸው አሰፋ በወታደሮች ላይ የበላይነት እንደያዙ እየተነገረ ነው።