(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 8/2010) በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የብሔረሰቦችን ተዋጽኦ መሰረት ያደረገ የስራ ቅጥር እንዲካሄድ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ።
አዋጁ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ፖልሲን ይቃርናል ተብሏል።
በወረቀት ላይ የሰፈረው ፖሊሲ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የሚኖር የምልመላና የእድገት ስራ በግለሰቡ ብቃት ላይና በዚሁ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያዛል።
አሁን ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ከዚህ በተለየ መልኩ በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የሚደረገው የስራ ቅጥር የብሔረሰቦችን ተዋጽኦ መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው።
ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ሊኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ሙያተኞች አሁን የቀረበው ህግ የፊዴራል የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲን የሚጥስ እንደሆነ ገልጸዋል።
በወረቀት ላይ ከሰፈረውና በግለሰቡ ብቃት ላይ ተመስርቶ ይካሄድ ከሚለው ፖሊሲ ጋር በፍጹም የማይገናኝ ነው ይላሉ አስተያየት ሰጭዎቹ።
በአሁኑ ሰዓት ይህንን መሰረታዊ መርሆ ለመጣስ የተፈለገው ሲቪል ሰርቪሱን በፖለቲካዊ አቋማቸው የገዢው ፓርቲ አባላት የሆኑትን ለመሙላትና የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆችን ለመጉዳት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የብሔረሰቦችን ተዋጽኦ መሰረት ያደረገ የስራ ቅጥር እንዲካሄድ የሚያስገድደው ረቂቅ አዋጅ በሃላፊነት ቦታዎች ስለሚኖረው የብሔረሰብ ስብጥር ግን ያነሳው ነገር የለም።
ረቂቅ አዋጁ ከዚህም ሌላ በሙስናና በአስገድዶ መድፈር ተሳታፊ ሆነው የተገኙና የተፈረደባቸው ግለሰቦች በመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች እንዳይቀጠሩ የሚያስገድድ ሀሳብንም አካቷል ።
በሙስና፣በእምነት ማጉደል፣በስርቆት፣በአስገድዶ መድፈር፣በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተፈረደበት ግለሰብ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ እንዳይሰራ የሚከለክለው ይህው ረቂቅ አዋጅ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የብሔረሰብ ተዋጽኦን ለማመጣጠን በሚደረገው ሒደት አነስተኛ ውክልና ያላቸውን በልዩ ድጋፍ ቁጥራቸውን ስለመጨመር ይዘረዝራል።
ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ የቀረበው ይህው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ለሴት ሰራተኞች በወሊድ ጊዜ ይሰጥ የነበረውን የሶስት ወራት ግዜ ወደ አራት ከፍ አድርጓል።