ኀዳር ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእየአመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ለማክበር መንግስት እስከ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ መረጃዎች አመለከቱ።
ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዝግጅቱን ከማቀድ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን የሚፈጽሙት ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። በኢትዮጵያ የሚከበሩ በአላትን እነዚህ ተቋማት ያለተቀናቃኝ በመውሰድ እየበለጸጉበት መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።
ኢህአዴግ ካወጣው መረሃ ግብር ለመረዳት እንደሚቻለው የዘንድሮው በአል ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችን ለህዳሴያችን፣ ህገመንግስታችን የህዳሴያችን የማእዘን ድንጋይ ነው፣ ህገመንግስት እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ማክበርና መስከበር የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው፣ የመለስ ሌጋሲን ጨብጠን የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን እናደርጋለን የሚሉ መለእክቶች ይተላለፉበታል።