የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ ከስልጣናቸው ተባረሩ

ኢሳት (ግንቦት 16 ፥ 2008)

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ ከስልጣናቸው ተባረሩ ፥ በምትካቸው አዲስ ሰው ተሹሟል። ባለቤታቸው በተመሳሳይ ከስራቸው ተነስተዋል።

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት 2ኛ ሰው የሆኑት አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ በዚሁ መስሪያ ቤት ከሚሰሩት ባለቤታቸው ጋር ከስራና ከስልጣን ከመነሳታቸው በተጨማሪ፣ በፀጥታ ሃይሎች ክትትል ውስጥ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

አቶ ኢሳያስን ተክተው ስፍራውን የያዙት አቶ ሃደራ አበራ የተባሉ በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ በሃላፊነት ስፍራ ላይ የነበሩ ግለሰብ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

አቶ ሃደራ አበራ በደርግ ዘመን በሻምበል ማዕረግ የሃገሪቱን ደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኛ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣም በስራቸው ቀጥለዋል። አቶ ሃደራ አበራ የትግራይ አድዋ ተወላጅ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

ስልጣናቸው ተነጥቀው ከሃላፊነት የተባረሩት አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ነባር የህወሃት ታጋይ ሲሆኑ፣ አሰቃቂነቱ የሚጠቀሰው ባዶ 6 ወህኒ ቤት በሃላፊነት ማገልገላቸውንም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። በአቶ ኩማ ደመቅሳ ስር የሟቹ የደህንነት ሃላፊ አቶ ክንፈ ገ/መድህን ረዳት ሆነው በሽግግሩ ዘመን አገልግለዋል።

በ1993 ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለሁለት ሲከፈል ከአቶ መለስ ጎን በመቆም፣ እንዲሁም በምርጫ 97 የቅንጅት መሪዎች ሌሎችንም የማሰር ኦፕሬሽን በመምራት የሚተቀሱት አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ በደንንነቱ ተቋም ውስጥ 2ኛው ሰው ሆነው ቢቀመጡም በአቶ መለስ የስልጣን ዘመን መጨረሻ ላይ ባሉት ሶስት አመታት ፣ በሃላፊነት ከተቀመጡት ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በላይ የመሪነት ሚና መጫወታቸውና ተሰሚነት እንደነበራቸው ምንጮች አስታውሰዋል።

ከአቶ መለስ ህልፈት በኋልም ከሟቹ ጠ/ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ቅርበት እንደነበራቸው የሚጠቀሱት አቶ ኢሳያስ ከስፍራቸው እንዲነሱ የተደረገው በዋና ሃላፊው በአቶ ጌታቸው አሰፋ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

የጸጥታ ሃላፊዎችን የመሻርም ሆነ የመሾም ስልጣን የጠ/ሚኒስቴሩ ቢሆንም፣ ያለእርሳቸው ዕውቅና እንደተባረሩም እኒሁ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የአቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ከስራና ስልጣን መባረርን ተከትሎ ከርሳቸው ባለቤት ውጭ በሌልች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ስለመኖሩ እስከአሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ግን ባለፈው ቅዳሜ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ አሜሪካ ገብተዋል።

ቅዳሜ ግንቦት 13/2008 አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ዳለስ አውሮፕላን ማረፊያ ከልጃቸው ጋር የደረሱት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ በካሜራ ዕይታ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የመጡበት ምክንያት አልታወቀም።