የቤተመንግስት ጠባቂዎችና የዶ/ር አብይ አጃቢዎች ተቀየሩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢህአዴግ ውስጥ የሚታየውን መከፋፈል እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ በቤተመንግስት ዙሪያ ጥበቃ የሚያደርጉ እንዲሁም ጠ/ሚኒስትሩን የሚያጅቡ ሰዎች እየተቀየሩ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከ20 አመታት በላይ የቤተመንግስት ዋና ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ገብረትንሳኤ ገብረሚካኤል ከስልጣናቸው ተወግደው በምትካቸው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ወርቅነሽ ብሩ መተካታቸውን የተዘገበ ሲሆን፣ ገብረትንሳይ ከስልጣን እንደተነሱ በእርሳቸው ስር የነበሩ ጠባቂዎችና አጃቢዎችም እንዲቀየሩ ተደርጓል።
ኢሳት ከተለያዩ የድርጅቱ ሰዎች ለማረጋገጥ እንደቻለው በኢዲሱ ጠ/ሚኒስትር አንዳንድ እርምጃዎች ያልተደሰቱ የህወሃት ነባር ተጋዮችና ወታደራዊ አዛዦች በጠ/ሚኒስትሩ ህይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ፍንጮች በማግኘታቸው የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪዎችና በቅርበት አብረዋቸው የሚሰሩ የስራ ባልደረቦቻቸው ጠባቂዎችና አጃቢዎቻቸው እንዲቀየሩላቸው ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ በፖሊስ እና በቤተ መንግስት ጥበቃ ላይ እያደረጉ ያለው ለውጥ ህወሃቶችን ማስቆጣቱንና ቅሬታቸውን ለጠ/ሚኒስትሩ እየገለጹ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።
ኦህዴድና ብአዴን እስከ መጪው ነሃሴ ድረስ አጠቃላይ መከላከያውና ደህንነቱ እንደገና እንዲዋቀር የሚፈልጉ ሲሆን፣ ህወሃት በበኩሉ ደህንነቱ እና መከላከያው ኢትዮጵያን ከውጭ ጥቃት በብቃት እየተከላከለ ያለ ተቋም በመሆኑ መነካት የለበትም የሚል አቋም ይዟል።
ጠ/ሚኒስትሩን የሚደግፉ የድርጅቱ አባላት የጠ/ሚኒስትሩ ደህንነት እያሳሰባቸው እንዲመጣ ሲገልጹ ቢቆዩም፣ አሁን እየተደረገ ያለው ለውጥ አንጻራዊ ደህንነታቸውን እንደሚያረጋግጥላቸው ይገልጻሉ።
እስካሁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሃድጎ ስዩም እና ግርማይ ከበደ ወይም ማንጁስ ከፌደራል ፖሊስ አዛዥነታቸው ተነስተዋል። በግርማይ ከበደ ቦታ የኦሮምያ ፖሊስ አባል የነበረው መላኩ ፈንታ ተተክቷል። በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የወንጀል ምርመራ ዋና ሃላፊ ረታ ተስፋዬ ተነስተው በአማራ ክልል ወንጀል ምርመራ ዘርፍን በረዳት ኮሚሽነር ማዕረግ ሲመሩ የነበሩት ተኮላ አይፎክሩ ተሹመዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይህደጎ ስዩም ወደ ፌደራል ፖሊስ ተዛውረው የሰው ሃብት ክፍል ሃላፊነት ቦታ ተመድበዋል።