የባንግላዴሽ አይሮፕላን በካታማንዱ ተከሰከሰ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 3/2010) ንብረትነቱ የባንግላዴሽ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በኔፓል መዲና ካታማንዱ ተከሰከሰ።

በትንሹ 40 ያህል መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ሕይወታቸው አልፏል።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በማረፍ ላይ እያለ መሆኑም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ትላንት ምሽት በኒዮርክ ከተማ አንድ ሔሊኮፕተር ተከስክሶ 5 ሰዎች ሞተዋል።

ንብረትነቱ የባንግላዴሽ አየር መንገድ የሆነ ቦባርዲየር ዳሽ ኤይት የበረራ ቁጥር ቢኤስ 211 የሆነው አውሮፕላን ከባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ መነሳቱንም ታውቋል።

አውሮፕላኑ በኔፓል ዋና ከተማ ካታማንዱ አውሮፕላን ማረፊያ ደቡባዊ ክፍል ላይ እንዲያርፍ የተፈቀደለት ቢሆንም በሰሜናዊው ጫፍ ላይ በማረፍ ላይ እያለ መከስከሱ ታውቋል።

ወዲያውኑም ቃጠሎ መነሳቱና ጉዳት መከተሉንም የኔፓል ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ከባንግላዴሽ ርዕሰ መዲና ዳካ ወደ ኔፓል ዋና ከተማ ካታምንዱ 415 ማይል ያህል የተጓዘው የበረራ ቁጥር ቢ ኤስ 211 አውሮፕላን በሃገሬው ሰአት አቆጣጠር ሰኞ ከሰአት በኋላ 8 ሰአት ከ20 ደቂቃ ላይ ሲከሰከስ 31 ተሳፋሪዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል።

9ኙ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር 50 ደርሷል ሲሉ ተደምጠዋል።

22 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ከቆሰሉት ውስጥ አንዳንዶቹ ጉዳታቸው የከፋ እንደሆነም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እሁድ ምሽት ኒዮርክ ከተማ ውስጥ አንድ  ሔሊኮፕተር ተከስክሶ አምስት ሰዎች ሞተዋል።

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ኢስት ሪቨር ላይ በተከሰከሰው የሔሊኮፕተር አደጋ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሲያልቁ ፓይለቱ ግን ተርፏል።

የአደጋ ጊዜ ዋናተኞች አደጋውን ተከትሎ ሰላባዎቹን ለማዳን የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ሕይወታቸውን ለማትረፍ ግን አልቻሉም።

የአደጋ ጊዜ ዋናተኞቹ ሶስቱን ተሳፋሪዎች ከነሕይወታቸው ከውሃ ውስጥ ማውጣት የቻሉ ቢሆንም ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ግን ሕይወታቸው አልፏል።

ፓይለቱ ራሱን ከአደጋው ማትረፉ ተመልክቷል።

የፌደራል የአቬሽን ባለስልጣን የአደጋውን መንስኤ እየመረመረ ይገኛል።

ሟቾቹ ሔሊኮፕተሩን በግል ተከራይተው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች እንደሆኑም ታውቋል።