ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)
በመቀሌ እግር ኳስ ቡድን እና ደጋፊዎች በደል ደርሶብን እያለ አለአግባብ የሆነ ውሳኔ ተወስኖብናል ያለው የባህርዳር ከነማ ክለብ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ።
የክለቡ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ በማምራት በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አንቀጽ 95 መሰረት አስተናጋጅ አገር እና ክለብ ወይም ደጋፊዎች ሲያጠፉ በፎርፌ ሊሸነፍ ሲገባ ውሳኔው የተገላቢጦሽ የባህርዳርን ክለብ የጎዳ ነው ሲሉ ይግባኝ አቅርበው ነበር።
ይሁንና ይግባኝ የቀረበለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ጽ/ቤት አነጋገሩ በሚል ውሳኔያቸውን እንደማይቀይሩ ገልጸዋል።
አመራሮቹ ግን ይግባኝ የሚመለከተው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንጂ የመንግስት አካል አይደለም ቢሉም ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በመጨረሻም እኛ የህዝብ አደረጃጀት ቢሮውን ጠይቀን ውሳኔውን አጽኑ ተብለናል በሚል የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ይግባኙን እንደማይቀበል በደብዳቤ አስታውቋል።
ደብዳቤውም ለአማራ እግር ኳስ ፌዴሬስን፣ ለክክሉ ስፖርት ኮሚሽንና ለባርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ በግልባጭ አሳውቋቸዋል።
ይህ በመሆኑም በቀድሞው ውሳኔ መሰረት ግንቦት 29 ፥ 2009 አም ጨዋታው በመቀሌ ስታዲየም ተመልካች በሌለበት በዝግ በድጋሚ እንዲካሄድ ክለቡ ወደዚያ እንዲያመራ ተፈርዶበታል።
የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎችና የአካባቢው ነዋሪውች ግን ክለቡ መቀሌ ሄዶ እንደማይጫወት ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውና ውሳኔው እንዳይቀበሉ ጥሪ እያስተላለፉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።