የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ የመቀሌ አቻው ለጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ባለመገኘቱ ፎርፌ እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበ

ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)

የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለተመሳሳይ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመቀሌ አቻው ውድድር ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ ፎርፌ እንዲሰጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን  ጠየቀ።

ክለቡ ከዚህ ቀደም በመቀሌ ከተማ ከዚሁ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ በተፈጠረ ግጭት ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥፋተኛ ተብሎ ተጫዋቾቹና ቡድን መሪዎቹ በገንዘብ መቀጣታቸው ይታወቃል ።

የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች በመቀሌው አቻው ደጋፌዎች ድብድባ ከደረሰባቸው በኋላ ከከተማ እንዲወጡ ተደርገው አውቶብሳቸውም ተሰባብሮ ወደ ክልላቸው የኋላ ኋላ ለመመለስ በቅተው ነበር ። ወደ ባህር ዳር ለመመለስ ሲሞክሩም በአገዛዙ የተመደቡ አንድ ቄስ በተሳፈሩበት መኪና ውስጥ ገብተው ሳትመረቁ አትሄዱም በሚል ለማስገደድ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እንደቀረ በወቅቱ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል ። 

በዚህ ሁኔታ የተቋረጠው ውድድር እንደገና ቀሪውን ጨዋታ ተመልካች በሌለበት በመቀሌ እንዲካሄድ ቢወሰንም ፌዴሬሽኑ ሃሳቡን በመቀየር በአዲስ አበባ ረቡዕ ዕለት በ21/10/2009 እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞ ነበር ። ይህንኑ መነሻ በማድረግ የባህር ዳር ከነማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝቶ በሜዳ ቢጠባበቅም መቀሌዎችና አወዳዳሪው አካል በስፍራው ሊገኙ አልቻሉም ። በዚህም ምክኒያት የባህር ዳሩ እግር ኳስ ክለብ የመቀሌ አቻው በውድድር ሜዳው ባለመገኘቱ ፎርፌ እንዲሰጠው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ደብዳቤ ጽፏል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ምንም እንኳ የባህርዳር ክለብ ጋር ተስተካካይ ጨዋታውን ለማካሄድ በሜዳ ቢገኝም በአዲስ አበባ ያለው የመቀሌ ቡድን ከሱሉልታ ጋር በነበረው ጨዋታ ፍጹም ቅጣት ሲሰጠው ሱሉልታዎች በመቃወማቸውና ለድብድብ በመጋበዛቸው ምክንያት ጨዋታው መቋረጡ ተነግሯል ። የመቀሌው ቡድን ቀደም ብሎ ከሱሉልታ ቡድን ጋር ጨዋታውን ለመካሄድ ሰኞ እለት የውድድር ፕሮግራም ከተያዘ በኋላ በሜዳ ችግር ሳይካሄድ በመቅረቱ  ቅሬታ ሲያቀርብ ነበር ።

የመቀሌው ከተማ እግር ኳስ ቡድን ፌዴሬሽኑ የሚያወጣው የውድድር ፕሮግራም ትክክል አይደለም በሚል ቅሬታ በደብዳቤ ሲያቀርብ  ሁኔታው ካልተስተካከለ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም መዛቱ ይታወሳል ። በከፍተኛ ሊጉ የዘንድሮው ውድድር የመቀሌ ከነማ እግር ኳስ ቡድን ከነበሩት 27 ጨዋታዎች ውስጥ 17 የፍጹም ቅጣት ምት በማግኘት ይህንኑ እድል በማግኘት ክብረ ወሰኑን ይዟል ።