የባህርዳር ከነማና የደሴ ከነማ ደጋፊዎች ተቃውሞአቸውን አሰሙ

የባህርዳር ከነማና የደሴ ከነማ ደጋፊዎች ተቃውሞአቸውን አሰሙ
(ኢሳት ዜና የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ/ም) ባለፈው ቅዳሜ የባህር ዳር ከነማ እና ደሴ ከነማ የእግር ኳስ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተመልካቾች አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮችን አሰምተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 10 “ በስፖርት ማዘውተሪያዎች ማዕከላት ከስፖርት ተግባር ውጪ የሆኑ ሁከቶችና ብጥብጦችን መፍጠር የተከለከለ ነው” ቢልም ተመልካቾች፣ ተቃውሞአቸውን ከመግለጽ ወደ ሁዋላ አላሉም።
ተመልካቾች “ ቢመችሽም፣ ባይመችሽም፣ አንች ወያኔ አለቅሽም፣ ወያኔ ሌባ፣ መሰናበቻ መሰናበቻ አሁን የቀረው ወያኔ ብቻ” የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች አሰምተዋል።
በፒክ አፑ መኪና ተጠግተው ከሚያልፉት ወጣቶች መካከል ወታደሮች ወደ መኪናችን ተጠጋህ በሚል አንዱን ወጣት መደብደባቸውን ተከትሎ “አትምታው” በሚል ተቃውሞ ተነስቷል።
በግርግሩ መካከል የተነሳውን ጩኸት የሰሙ ወጣቶች በአካባቢው ያገኙትን ድንጋይ በመያዝ እየወረወሩ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ፣ ወታደሮች በጉዳዩ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸውን ተመልካቾች እና በፊት ለፊት የሚገኙ የከተማዋን ነዋሪዎች ጨምር በ ዱላ በመደብደብ በህዘቡ ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
በህዝብ መካከል ገብቶ በመደባደብ ላይ የነበረን የአገዛዙ ወታደር ወጣች ጎትተው ዱላውን በማስጣል በራሱ ዱላ ሲመቱት እንደነበር በአቅራቢያው የነበሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በተለያዬ አቅጣጫ በመበታተን አካባቢውን ቢለቁም፣ ወታደሮች የጪሰ ቦንብ በመያዝ መንደር ለመንደር በማባረር ጉዳት ሲያደርሱ ታይተዋል፡፡አሰሳው ምሽትም በመቀጠል በአገዛዙ ወታደሮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የጠረጠሯቸውን ወጣቶች ለማሰር ተንቀሳቅሰዋል።