ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዲያስፖራ ቀንን ለማክበር በባህርዳር የተገኙት 50 የዲያስፖራ አባላት፣ በመንግስት ወጪ ባረፉበት ኢትዮ-ስታር ሆቴል በቢንቢ ትንኝ መበላታቸውን እንዲሁም የተመቻቸ ምግብ አልቀረበልንም የሚል ምክንያት በመጥቀስ፣ ቁርስና ምሳ አንበላም ብለው አድማ ያደረጉ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ክልሉ በመደወል እንግዶቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወደ ሚያርፉበት ጣና ሆቴል እንዲዛወሩ ተደርጓል። የመስተዳደሩ ባለስልጣናት የሆድ ጥያቄ የሚያነሱ ዲያስፖራዎች በሚል ትችት ማቅረቡን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጻለች።
ክልሉ ለዲያስፖራ አባላቱ የመኝታ፣ የምግብ፣ የጉዞና ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም ለሽልማት ካዘጋጀው ቦታ ጋር በጠቅላላ 30 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ማውጣቱን ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ የዲያስፖራ አባላቱ በመንግስት ወጪ ሲዝናኑ ቆይተው ክልሉ ያዘጋጀውን የ1 ሺ ብር ቦንድ እንኳ ሳይገዙ መሄዳቸው መስተዳድሩን በእጅጉ አበሳጭቷል።
የዲያስፖራ አባላቱ በ12 ተደራጅተው 80 ሺ ብር ካስያዙ ቦታ እንደሚሰጣቸው መገለጹን ተከትሎም ፣ የከተማው የመንግስት ሰራተኞች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። በአዳማ ተዘጋጅቶ በነበረው የዲያስፖራ በአል ላይም ዲያስፖራው ቦንድ ለመግዛት ባለመቻሉ አዘጋጆች ቅር ተሰኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የዲያስፖራ ማሰተባሪያ ዳይሬክቶሬት፣ የዲያስፖራ ተቃውሞን ማብረድ ትልቅ ግብ መሆኑን በማየት ተሳትፎቸው ላይ ተፅኖ አታሳርፉ ሲል ለአማራ እና ለኦሮምያ ክልል አቅጣጫ ሰጥቷል።
በባህርዳር በ25 ሰዎች የተደራጁ 3 ሺ 725 ቤት ፈላጊዎች 60 ሺ ብር በዝግ አካውንት አስቀምጠው ለአመታት ቦታ አጥተው በተቀመጡበት ወቅት፣ የዲያስፖራ አባላቱ 80 ሺ ብር አስይዙና ቦታ በአፋጣኝ ይሰጣችሁዋል መባላቸው፣ የመንግስት ሰራተኞችን ያበሳጨ ጉዳይ ሆኗል።