ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ቡና ምርትዋ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በ2004 በጀት ዓመት ባለፉት 11 ወራት ለውጪ
ገበያ ያቀረበችው ቡና ለመላክ ከታሰበው ገቢ ጋር ሲነጻጸር መቀነሱ ታወቀ፡፡
ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው የአገሪቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚነገርለት ቡና በ11 ወራት ውስጥ ያስገኛል ተብሎ ከተጠበቀው ጋር ሲነጻጸር ያስገኘው 67 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡በተጠቀሱት ጊዜያት 261
ሺ27 ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 6 በሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ቢያዝም ማግኘት የተቻለው 140 ሺ212 ቶን በመላክ 714 ሚሊየን ዶላር ነው፡፡
በጠቅላላው በግብርና ምርቶች የ11 ወራቱ የዕቅድ አፈጻጸም በመጠን 71 በመቶ፣በገቢ 73 በመቶ ብቻ በመሆኑ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ ጋር ሲተያይ ደካማ ነው፡፡
በተለይ ለቡና ኤክስፖርት አፈጻጸም ማነስ በምክንያት ከተጠቀሱት መካከል የተወሰነ የቡና ክምችት ያላቸው ላኪዎች ከክምችታቸው አንጻር በቂ ሸያጭ መፈጸም አለመቻላቸው፣የዓለም አቀፍ ቡና ገበያ ዋጋ ተለዋዋጭነት ጋር ተያይዞ በቡና ገዥዎች የሚቀርበው የግዥ ጥያቄ ውስን በመሆኑ የተላከው ቡና ዝቅተኛ መሆን ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም አቅራቢዎች ባለፈው ዓመት ዋጋ ላይ በመንተራስ በከፍተኛ ዋጋ ግዥ በመፈጸማቸውና የዓለም የቡና ዋጋ በመቀነሱ ከአቅራቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ለዓለም ገበያ ማቅረብ መቸገራቸው የሚሉት ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡
የሸቀጦች ልውውጥ ገበያ ዋና ስራአስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ኢሌኒ ገብረመድህን በቅርቡ ሀላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ማስታወቃቸው ይታወቃል። ብዙዎች ስራአስኪያጁዋ ስልጣናቸውን የለቀቁት ከቡና ገቢ ማሽቆልቆል ጋር በተያያዘ ነው በማለት አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide