ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በጌዲዮና በሲዳማ ዞን በቡና ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለዘጋቢያችን እንደገለጡት የቡና ገበያ መቀዝቀዙ ለኪሳራ እየዳረጋቸው ነው።
በ2004 ዓም በእረጥብ ቡና ግዢና በደረቅ ቡና መፈልፈያ የሳይት የቡና ማሽን የተከሉ ባለሀብቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ ኪሳራ በ2005 ነሀሴ ውር መጀመር የነበረበት የቡና ማሽኖች እድሳትና የቡና ማድረቂያ አልጋ ስራ እስካሁን አለመጀመሩ በአጠቃላይ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
በሲዳማ ዞን በጥቅምት ወር የቡና ግዢ የሚጀመርበትና ማሽኖች ስራ የሚጀምሩበት ወቅት ቢሆንም ፣ በዚህ አመት ግን በጥቅምት ማሽኖች እንኳ ዝግጁ አለመሆናቸው በገበሬው ፣በነጋዴውና በማህበረሰቡ ላይ ኪሳራ ያስከትላል በማለት ነጋዴዎች ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።
በሲዳማ ዞን ከ400 በላይ የቡና ሳይቶች ያሉ ሲሆን እስካሁን ስራ የጀመሩት በበልሳ ወረዳ የሚገኙት 2 የቡና መፈልፌአዎች ብቻ ናቸው። በጌዲዮ ዞንም እንዲሁ የቡና አቅራቢ ነጋዴዎች እስካሁን ስራ አለመጀመራቸው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
በተያያዘ ዜና በሲዳማ ዞን ውስጥ በተለያየ ሙያ ማለትም በነርስንግ፣ ህግና በመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች ተምረው የተመረቁ ተማሪዎች ስራ በማጣታቸው በተለያዩ የወረዳ አስተዳደሮች በመቅረብ በሚያሰሙት ቅሬታ ችግር ውስጥ የገባው መስተዳደድሩ ተማሪዎች በዞኑ የህብረት ስራ ማህበራት በመቅረብ የ4 ቀን ስልጠና በመውሰድ ወደ ቡና ግዢ እንዲሰማሩ በየሳይቶቹ ተደልድለዋል።