ታህሳስ ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ተማሪዎቹ ባለፈው አርብ ምሽት በጀመሩት ተቃውሞ የመማሪያ ክፍሎች መስኮቶች መሰባበራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
አረብ ምሽትና ቅዳሜ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዩኒቨር ስቲውን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን ገሚሶቹ በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ተጠልለው እንደነበር ታውቋል።
ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን ያሰሙት አዲሱን የውጤት አሰጣጥ ፖሊሲ በመቃወም እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስላልተሟሉላቸው ነው። በግቢው ውስጥ 2 ሺ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የውሀና የመጸዳጃ እጥረት አለ። አብዛኞቹ ተማሪዎች የሀይላድ ውሀ እየገዙ እንደሚጠቀሙና በየጫካው ለመጸዳዳት እንደተገደዱ ታውቋል።
ዩኒቨርስቲው አንድ ቤተመጽሀፍ ብቻ ያለው ሲሆን፣ በቂ መጽሀፎችም እንደሌሊት ተማሪዎች ይናገራሉ። 95 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ብቻ “ኤ” እንዲያገኙ የሚያስገድደው አዲሱ መመሪያ ተማሪዎችን አስቆጥቶ ወደ አደባባይ እንዳስወጣቸው ታውቋል።
ከ300 በላይ ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ አንማርም በማለት ዩኒቨርስቲውን ጥለው ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በትናንትናው እለት ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በተገባላቸው ቃል መሰረት ወደ ግቢያቸው መመለሳቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ትምህርት አለመጀመራቸው ታውቋል።
ከሳምንት በፊት አዲሱን የውጤት አሰጣጥ መመሪያ በመቃወም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ለማሳማት ውስጥ ለውስጥ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ መንግስት መመሪያውን ተግባራዊ እንዳማያደርገው ቃል በመግባቱ እንቅስቃሴው ሊቆም እንደቻለ ታውቋል።
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ በቦረና ዞን እንደሚገኝ ይታወቃል።