የቆዳ ፋብሪካዎች የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት ችግር ገጥሞናል አሉ።

(ስምንት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ያሉት የቆዳ ፋብሪካዎች የግብዓት ፍላጎታቸው በዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ የበግና ፍየል ሌጦና ከ2 ሚሊየን በላይ የበሬ ቆዳ ሲሆን፥ እየቀረበላቸው ያለው የቆዳ መጠን  ከ16 እስክ 17 ሚሊየን ሌጦ እና በቆዳ ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በታች ነው።

ከዚህ በመነሳት ሃገሪቱ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ገቢ ማሳካት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ የሚናገሩት።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ቆዳ ፋብሪካዎቹ የሚፈልጉትን የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት የሚያገኙት 20 በመቶውን ከቄራዎች  የተቀረውን 80 በመቶ ደግሞ ከህብረተሰቡ ሲሆን ፥ ህብረተሰቡ እንስሳትን የሚያርደው በአመዛኙ የበዓል ወቅቶችን እየጠበቀ በመሆኑ አብዛኛዎቹ የቆዳ ፋብሪካዎች አቅማቸውን ሙሉ ተጠቅመው መስራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ስዓትም ከግማሺ በላይ የሚሆኑት የቆዳ ፋብሪካዎች በጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት ችግር ስራ አቁመዋል።

አቶ ወንዱ  ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ባሁኑ ወቅት ፋብሪካዎቹ የቆዳ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከሃገር ውስጥ የአቅርቦት አቅም ከመውጣታቸው ባለፈ፥  ወደፊት ይገነባሉ ተብሎ የሚጠበቁት የቆዳ ፋብሪካዎችም አቅርቦቱን የማግኘታቸው ተስፋ እጅግ የተሟጠጠ ነው።

በእንስሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነቸውን ሃገራችንን ተሻግረው ጥሬ ቆዳና ሌጦ ፍለጋ ወደ ውጭ ገበያ መመልከት የጀመሩ ድርጅቶች መኖራቸውንም ሀላፊው ጠቁመዋል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ሃይሌ ለፋብሪካዎቹ ከሚቀርበው ቆዳ ውስጥ 65 በመቶው ጥራት የጎደለው በመሆኑ ይጣላል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 42 በመቶው ችግር የሚደርሰው በእንስሳቱ የውጭኛው የቆዳ ክፍል ላይ ነው ብለዋል።80 ዓመታትን  ያስቆጠረው  የኢትየጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከ30 ያልበለጡ ፋብሪካዎችን አቅፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ዘርፉ በአማካይ በዓመት 123 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያስገኛል።