የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት ቅዱስ ሲኖዶሱ ቢወስንም ተግባራዊ አልሆነም ተባለ

ሐምሌ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ተማሪዎቹ ያነሷቸውን ጥያቄዎች የተመለከቱት  ፓትሪያሪኩ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በኮሌጁ ይሰጥ የነበረው የትምህርት እና የምግብ አገልግሎት እንዲቀጥል እና ተመራቂ ተማሪዎችም በወቅቱ እንዲመረቁ የወሰኑ ቢሆንም ተማሪዎቹ ግን እስከትናንት ድረስ ትምህርት አለመጀመራቸውን ተማሪዎቹን አነጋግሮ ሰንደቅ ዘግቧል።

የተማሪዎች መማክርት ሰብሳቢው ዲያቆን ታምርአየሁ አጥናፌ ለጋዜጣው እንደገለጸው፣ ሐሙስ እለት ውሳኔውን ሰምተው ቢሄዱም ጊቢው ውስጥ ግን የተለወጠ ነገር አልነበረም፣ ተማሪዎቹም መመገብ አልጀመሩም።

ንቡረ እድ ኤልያስ ግቢውን ተረክበው ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን ቢሰሙም  ንቡረእዱ ተማሪዎቹን ባነጋገሩበት ወቅት፣  ምግቡም እንዲጀመር፤ ትምህርትም እንዲቀጥልና የሚመረቀውም እንዲመረቅ ለማመቻቸት እንጂ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንደሌላቸው በመግለጻቸው ተማሪዎች ጥያቄያችን አልተመለሰም የሚል ቅሬታ እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው ዲያቆን ታምራየሁ ለጋዜጣው ገልጿል።

ተማሪዎቹ ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መመለስና አለመመለሳቸውን እንደማያውቁ ሰብሳቢው ተናግሯል።

የተወሰኑትን ውሳኔዎች በሰሚ ሰሚ እየሰሙ እንደሆነ የሚናገረው ዲያቆን ታምርአየሁ፤  ለጊዜው ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ የተለጠፈው ደብዳቤ ውድቅ ሆኖ ትምህርት እንደሚጀምር እና ተማሪዎችም እንደሚመረቁ ውሳኔ መተላለፉንም ጠቁሟል።

የኮሌጁ ተማሪዎች ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓም በኮሌጁ የሚታዩ የተለያዩ ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ጥያቄዎችን ይዘው ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ማምራታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ቅዱስ ፓትሪያሪኩ እና ቅዱስ ሲኖዶሱ ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ሲያነሷቸው የነበረውን ጥያቄዎች እውነተኛ መረጃ እንደሚያውቋቸው እና እነርሱ ጋር እንዳልደረሱ መግለፃቸውን ሰብሳቢው ለጋዜጣው ገልጿል።