የቅማንትን የመብት ጥያቄ ባነሱ ግለሰቦች ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2010) በህወሃት በተደራጁና የቅማንትን የመብት ጥያቄ ባነሱ ግለሰቦች ግጭት መቀስቀሱ ተገለጸ።

በጭልጋ ሀሙስ ገበያ በተባለ አካባቢ ከትላንት ምሽት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

ፋይል

የአማራ ክልል ምክር ቤት በተያዘው ሳምንት 69 ቀበሌዎች በቅማንት አስተዳደር ስር ልዩ ወረዳ መዋቅር ይዘው እንዲካለሉ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም የሚገባን የዞን መዋቅር ነው ባሉ ግለሰቦች ግጭቱ መቀስቀሱን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

ከህወሀት የድጋፍ ደብዳቤ የያዙት እነዚህ ግለሰቦች መተማ፣ ቋራ፣ ከምዕራብና ታች አርማጭሆ የተወሰኑ ቀበሌዎች ላይም የይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሁለቱም ወገኖች ስለአንድነት እንጂ ስለልዩነት አንስተው አያውቁም። ለዘመናት እንደአንድ ሆነው ኖረዋል።

ተጋብተው ተዋልደው ቤተሰብ መስርተው አብረው ዘልቀዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሁለቱን ወገኖች ሰላም የሚያደፈርስ፣ አብሮነታቸውን የሚያናጋ ችግር ተከስቷል።

ከሁለቱ ወገኖች ፍላጎት ውጪ በሶስተኛ ወገን የተስፋፊነት ህልም በመነጨ የተፈጠረው ችግር ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች ሞት፣ የአካል መጉደልና የንብረት ውድመት መከሰት ምክንያት ሆኗል።

የቅማንት የመብት ጥያቄ የተጫረው የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄን አንስተው ወደ ተጠናከረ ትግል መግባቱን ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይም የ50ሺህ ህዝብ ፊርማ አሰባስበው እንቅስቃሴ የጀመሩ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ተጽእኖአቸው እየጎላ ሲመጣ ይህን ጥያቄ የሚያደበዝዝና የሚቀለብስ አጀንዳ እንዲከፈት መፈለጉን ነው ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች የሚገልጹት።

ባለፉት ሁለት አመታት የቅማንት ጥያቄ ባልተለመደ መልኩ ከሁለቱ ወገኖች ደም ማፋሰሱ ያሰጋቸው የሀገር ሽማግሌዎች ችግሩን ተወያይተው ለመፍታት ሲያደርጉ የነበሩትን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በህወሀት በኩል መጠነ ሰፊ የማዋከብና የማስተጓጎል ርምጃ መወሰዱም ይገለጻል።

42 ቀበሌዎች ያለህዝቡ ፍቃድ በህወሀት አስገዳጅ መመሪያ በቅማንት አስተዳደር ስር እንዲካለሉ ከተወሰነ በኋላ በ12 ቀበሌዎች ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ህዝቡ በቀደመው መዋቅር እንቀጥላለን ማለቱም የሚታወስ ነው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ሰሞኑን ተሰብስቦ ለችግሩ መፍትሄ ነው ያለውንና 69 ቀበሌዎች በቅማንት ልዩ ወረዳ እንዲካለሉ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አዲስ ውዝግብ መቀስቀሱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በህወሀት ድጋፍ የቅማንት ኮሚቴ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ተጨማሪ አካባቢዎችን በመጠየቅ የዞን አስተዳደር መዋቅር ይገባናል ብለው መነሳታቸውን ተከትሎ ግጭት መፍጠሩን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የዞን መዋቅሩ መተማን፣ቋራንና ከወገራና አርማጭሆም የተወሰኑ ቀበሌዎችን በማካተት በቅማንት አስተዳደር ስር እንዲሆን የሚጠይቁት በህወሃት ተደራጁ የተባሉት ግለሰቦች በአካባቢው ከሚገኘውና በኮለኔል ፍትዊ የሚመራ የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ለማወቅ ተችሏል።

ህውሀት የታላቋን ትግራይ ካርታ እውን ለማድረግ መተማን ጨምሮ የተወሰኑ የጎንደር አካባቢዎችን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ጋር እንዲያገናኙ በማድረግ ያካለላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የዞኑን ጥያቄ እንዲያራግቡም የቅማናንት ኮሚቴ አባላት ከአቶ አዲሱ ለገሰ ጋር በጎንደር ጎሀ ሆቴል ሲመካከሩ እንደነበርም የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በጭልጋ ሀሙስ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ እንደአዲስ የተቀሰሰውን ግጭት ተከትሎም የአማራ ክልል ልዩ ሃይል መግባቱ የተገለጸ ሲሆን በትክል ድንጋይም ተመሳሳይ ውዝግብ እንዳለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ለኢሳት መረጃውን ያደረሱ የሀገር ሽማግሌዎች የህወሀትን ሴራ ለማክሸፍ ሁለቱም ወገኖች ከግጭት ራሳቸውን እንዲያርቁ ጥሪ አስተላልፈዋል።