(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)
በወልዲያ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በአል ላይ የመከላከያ ሰራዊት እንዳይገኝ ከተስማማን በኋላ ሰራዊቱ በበአሉ ስፍራ መገኘቱ ለግጭቱ መከሰት ምክንያት መሆኑን ብጹእ አቡነ ኤርሚያስ ገለጹ።
ሆን ተብሎ የታቀደ ይመስላል ሲሉም ሲሉም ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎና ከሚሴ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤርሚያስ ከግድያው ባሻገር ለንብረት ውድመቱም ምክንያት የሆነው የመከላከያ ሰራዊቱ መግባት እንደሆነ መናገራቸውን ሃራ ተዋህዶ ዘግቧል።
ከበአሉ አስቀድሞ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ከተማዋ እንዳይገባ ከዞን አመራር ጋር ሃገረ ስብከቱ መስማማቱን ያስታወሱት ብጹእ አቡነ ኤርሚያስ በዚህም “ወጣቱን አሳበዱት፣በጥይትም ለቀሙት” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
በማግስቱ ለተከተለው ግጭትና ውድመትም “የእነርሱ መዘዝ ነው፣እኛ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ምንም ነገር የለም” በማለት ለተከሰተውና ለቀጠለው ሁኔታ ወጣቱ ያጠፋው ጥፋት እንደሌለም መስክረዋል።
ድርጊቱ ሆን ተብሎ የታቀደ ሳይሆን እንዳልቀረም ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
ድርጊቱ የበቀል ይመስላል ማለታቸውም ተመልክቷል።
“ለምን እንደመጡ አናውቅም ሆን ብለው ለመምታት ይመስላል፣ከመካከላቸውም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል”ማለታቸውን ሐራ ተዋሕዶ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዙሪያ ዘገባ የሚያቀርበው ይህው ድረ ገጽ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ስለነበረው ስብሰባ የተናገሩትንም አስፍሯል።
አቶ ገዱ ሰራዊቱ ከከተማው እንደሚወጣና ተጠያቂውም ለፍርድ እንደሚቀርብ ቃል እንደገቡላቸው አስረድተዋል።
የጸጥታ ሃይሎች ቅዱስ ታቦቱን ባከበሩ ቀሳውስት ላይ ጭምር አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።
ከጎናቸው ባሉት ካህናት ባይደገፉ ኖሮ ወድቀው ነበር ያሉት አቡነ ኤርሚያስ ይህም ድርጊት ቤተክርስቲያኒቱን ጭምር መድፈር በመሆኑ መንግስት ድርጊቱን በማውገዝ የዕምነቱን ተከታዮች ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስበዋል።
ለሟች ቤተሰቦች የደም ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም ግድያው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡና ግድያውን የፈጸሙ ብሎም ጉዳዩን በቸልታ የተመለከቱ የዞኑ ባለስልጣናት በህግ እንዲጠየቁ ብጹእ አቡነ ኤርሚያስ ጥሪ አቅርበዋል።
እየተፈጸመ ያለው የግፍና የጥፋት ድርጊት ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ መሆኑ እጅግ እንዳሳዘናቸው የተነገሩት የሰሜን ወሎና የከሚሴ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ኤርሚያስ “ተው ማለት ያለበትም ሆነ ይህን ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው” ሲሉም ለሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።
በወልዲያው ግጭት ከተገደሉት 13 ሰዎች ውስጥ የ9 አመቱ ዮሴፍ እሸቱ የተባለ ሕጻን እንደሚገኝበትም ታውቋል።