የቂሊንጦ እስረኞች የግዳጅ የጉልበት ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቂሊንጦ እስር ቤት የግዳጅ የጉልበት ስራ እያሰራቸው መሆኑን በአርበኞች ግንቦት 7 ስም ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት እነ ጌታሁን በየነ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ እስረኞቹ ፣ 200 ኪሎ ግራም ቆሻሻና የ125 እስረኞች የሚቀርብን ወጥ ሁለት ሰዎች ብቻ እንዲሸከሙ እንደሚገደዱና ይህም በህገ ወጥ መንገድ ያለ አቅማቸው የግዳጅ ስራ እንዲሰሩ ከመገደዳቸውም ባሻገር ለጤና ጉዳት ተዳርገናል ይላሉ፡፡ እስረኞች ያለ ፈቃዳቸውና ያለ አቅማቸው የግዳጅ የጉልበት ስራ ለመስራት የማይገደዱ መሆኑ በግልፅ በህግ የተደነገገ መሆኑንና በቂሊንጦ እስር ቤት በፈቃደኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ እስረኞች እንደነበሩ ገልፀው፣ ፍርድ ቤቱ ቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞችን በግዳጅ ማሰራቱን እንዲያቆም ትዕዛዝ እንዲጽፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
የቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞችን ቆሻሻ እንዲደፉና የእስረኛውን ምግብ እንዲያመጡ በተራ በግዳጅ ከማሰራቱም ባሻገር፣ በእስር ቤቱ አስተዳደሮች ዘንድ ህገ ወጥ ነው የተባለ ተግባር ፈፅመዋል የተባሉ እስረኞችን በጉልበት ስራ እየቀጣ ይገኛል፡፡ የሱቅ እቃዎችን ለማስመጣትም እስረኞችን የሚያሸክም ሲሆን፣ አሁን ዞን 5 እየተባለ የሚጠራው የእስር ቤቱ ክፍል እስረኞች በግዳጅ የሰሩት ነው፡፡ በህጉ መሰረት አንድ እስረኛ የግዳጅ ስራ ሊሰራ የሚችለው ፍርድ ቤቱ ስራን እንደቅጣት አብሮ ከወሰነ ብቻ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው በቅድሚያ እስረኛው የተጠረጠረበትን ወንጀል ተጠይቆ ስለሆነ እና እነሱም የሽብር ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ በክሳቸው ምክንያት የህክምና አገልግሎት እንደሚነፈጉም ገልፀዋል፡፡