የቁጫ ወረዳ ችግር ተባብሷል ቀጥሎአል

ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ ከመብት ጋር በተያያዘ የሚደርሰው ስቃይ እንደቀጠ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በፖሊሶች ወከባ የተነሳ አንዳንድ ነዋሪዎች ሌሊቱን የሚያሳልፉት  ጫካ ውስጥ ነው። ፖሊሶች ሌሊት ቤት እያስከፈቱ እንደሚፈትሹ ነዋሪዎች ይናገራሉ

ከአንድ አመት በላይ በዘለቀው የቁጫ ችግር  ከ40 በላይ የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ  ወጣቶችም ታስረው ይገኛሉ። ከሰኔ ወር 2005 ጀምሮ እየተባባሰ ለመጣው የቁጫ ህዝብ የመብት ጥያቄ ገዢው ፓርቲ በጠረጴዛ ዙሪያ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ በጅምላ እያፈሱ መብት ጠያቂዎችን ወህኒ ማውረድን አማራጭ አድርጎታል በማለት አንድነት ፓርቲ ከሶስት ሳምንት በፊት  ጋዜጣዊ መግለጫ  መስጠቱ ይታወቃል።

ከ1 ሺ 15 በላይ የቁጫ ህዝብ በወህኒ ቤት መገኘቱን እንዲሁም አቶ ዛራ ዛላ የተባሉ አባወራ በአንድ የወረዳ ፖሊስ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን ፓርቲው ገልጾ ነበር ፡፡አንድነት በቁጫ ህዝብ የደረሰውን ዘግናኝ የመብት ረገጣ የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን እንዲቋቋም ቢጠይቅም እስካሁን መልስ አልተሰጠውም።