ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የቀብር ስነስርዓት በአሜሪካ ግዛት ተፈጸመ። በ77 አመታቸው ማክሰኞ ህዳር 27 ቀን 2009 አም በዩኤስ አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ያረፉት የአቶ ተስፋዬ ዲንቃ የቀብር ስነስርዓት ቅዳሜ ታህሳስ 1 ቀን 2009 ዓም በፌየር ፋክስ ሜሞሪያል ፓርክ ተፈጽሟል።
የቀድሞው የደርግ/ኢህድሪ መንግስት ውስጥ የንግድ፣ እንዲሁም የገንዘብና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ከሶስት በላይ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት ማገልገላቸው፣ በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን መሾማቸውን በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ከተነበበው የህይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።
የአራት ልጆች አባትና የ4 ልጆች አያት ናቸው። አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከአባታቸው አቶ ዲንቃ ያደሴ እና ከወ/ሮ አቦነሽ አየለ እ.ኤ.አ. በ1939 በወቅቱ አጠራር በሸዋ ክፍለሃገር አምቦ ከተማ መወለዳቸው ተመልክቷል።
“ከጭፍንና አክራሪ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና ዝንባሌዎች የራቁ ብሩህ አዕምሮና ዕርጋታን የተላበሱ ነበሩ” በሚልም በህይወት ታሪካቸው ላይ ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት እንዲጠናከር የሃገሪቱ ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲከበርና የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጥቅም እንዲጠበቅ የሰሩ መሆናቸውንም በቀብሩ ስነስርዓት ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።