የቀድሞ መንግስት ባለስልጣን የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነባቸው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)

በቀይ ሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በኔዘርላንድ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞ መንግስት ባለስልጣን የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነባቸው።

በደርግ ዘመነ መንግስት በጎጃም ክፍለ ሃገር የደርግ ተጠሪ በነበሩበት ወቅት ለ75 ሰዎች መገደልና ለ200 ሰዎች መሰቃየት ተጠያቂ የተባሉት አቶ እሸቱ አለሙ ዘ ሔግ ኔዘርላንድ ውሳኔው የተላለፈባቸው ትላንት ሀሙስ መሆኑም ታውቋል።

የ63 አመት እድሜ ያላቸው አቶ እሸቱ አለሙ በኔዘርላንድ ጥገኝነት አግኝተው መኖር የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990 ጀምሮ መሆኑ ተመልክቷል።

በቀረበባቸው ጥቆማና በተካሄደባቸው ምርመራ መሰረት ላለፉት ሁለት አመታት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ በወህኒ ቤት የቆዩት አቶ እሸቱ አለሙ ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ሆኖም የኔዘርላንድ የአለም አቀፉ የወንጀል ተከታታይ ቡድን ባካሄደው ምርመራና ከአይን ምስክሮች ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል በይኗል።

ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎ ዘሔግ ኔዘርላንድ የተሰየመው ችሎት በአቶ እሸቱ አለሙ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ወስኗል።

አቶ እሸቱ አለሙ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሌሉበት የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ቀደም ቀልቤሳ ነገዎ የተባሉ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣን አሜሪካ ላይ ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወሳል።

ከፈለኝ አለሙ የተባሉ ሌላ የደርግ ባለስልጣን አሜሪካ ዴንቨር ውስጥ ተይዘው የ22 አመት እስራት ተበይኖባቸዋል።

ይህም እስራት በተሳሳተ ማስረጃ ዜግነት መውሰዳቸውን ተከትሎ የተወሰደ ርምጃ መሆኑም ታውቋል።

የ62 አመቱ አቶ ከፈለኝ አለሙ የ22 አመት እስራታቸውን ሲጨርሱ በፈጸሙት ወንጀል እንዲጠየቁና ወደ ኢትዮጵያም እንደሚባረሩ ዘገባው አመልክቷል።