የቀድሞው የቻድ ፕሬዝዳንት የዘረፉትን ገንዘብ ሊመልሱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 2/2010)

የቀድሞው የቻድ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሀብሬ የዘረፉትን ገንዘብ ለማስመለስ የአፍሪካ ህብረት ጥረት መጀመሩ ታወቀ።

በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ለተገደሉና ለተሰቃዩ ሰለባዎች ማቋቋሚያ ከቀድሞ አምባገንን መሪ እንዲከፈል መወሰኑም ታውቋል።

ገንዘቡ ገቢ ባለመሆኑም ሀሰን ሀብሬን ወደ ስልጣን እንዲወጡ ያገዙት ፈረንሳይና አሜሪካም ለማቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደረጉ እየተጠየቁ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

በሴኔጋል ዳካር ያለጠያቂ ለ25 አመታት ያህል በተንደላቀቀ ሕይወት የቆዩት ሀሰን ሃብሬ ሰለባዎቹ ኣንዲሁም የቻድ አክቲቪስቶች ባደረጉት የ25 አመታት ጥረት በሴኔጋል ውስጥ በቁም እስር ላይ ቆይተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ከሴኔጋል ጋር በጥምር ባቋቋሙት ፍርድ ቤትም ቀርበዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ ወህኒ ወርደው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ሀሰን ሃብሬ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 30/2016 እንዲሁም በእሳቸው የአገዛዝ ዘመን ሰለባ ለሆኑ ለ7ሺ 346 ሰዎች ካሳ እንዲሆን 153 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉም ተወስኖባቸዋል።

የቻድ የቀድሞ አምባገነን መሪ ሀሰን ሃብሬ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 1/1990 ስልጣናቸውን ተነጥቀው ወደ ሴኔጋል ከመሸሻቸው በፊት 150 ሚሊየን ዶላር የሃገሪቱን ሃብት በቼክ ወራሳቸው የባንክ ሒሳብ ማዛወራቸው ተገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1982 እስከ 1990 ለ8 አመታት ቻድን የገዙትና ለ40ሺ ሰዎች ዕልቂትና ለ54ሺ ሰዎች ሰቆቃ ተጠያቂ የሆኑት የቻድ የቀድሞ አምባገነን መሪ ሃሰን ሃብሬ በሴኔጋል ዳካር በተሰየመ የአፍሪካ ሕብረትና ሴኔጋል ልዩ ችሎት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

የ153 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

በሽምቅ ውጊያ ስልጣን ይዘው በመንግስት ግልበጣ ስልጣናቸውን ያጡት ሀሰን ሃብሬ ተሸንፈው ሃገሪቱን ሲለቁ ከሃገሪቱ ግምጃ ቤት 5 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወስደዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀድሞው የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን በስጦታ ያገኙትን አንድ ሚሊየን ዶላር ጨምሮ ሌላ የሰበሰቡን ገንዘብ ለማስመለስና ለሰለባዎቹ ካሳ ለማስከፈል ጥረት ቢደረግም ማግኘት የተቻለው ገንዘብ ግን የተወሰነው ብቻ እንደሆነም ተመልክቷል።

በመሆኑም ፈረንሳይና አሜሪካ ሃሰን ሀብሬን ወደ ስልጣን በማምጣት ረገድ በተጫወቱት ሚና ሳቢያ ለሰለባዎቹ ካሳ እንዲከፍሉ እየተሞከረ ሲሆን ከእድሜ ልክ ፍርደኛውም የ74 አመቱ ሃሰን ሃብሬን የባንክ ተቀማጭና ንብረቶችን ማሰሱም ቀጥሏል።