የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ እና ግብረአበሮቻቸው ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርምራ ጊዜ ተሰጠባቸው።
( ኢሳት ዜና መስከረም 04 ቀን 2011 ዓ/ም ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ አብረዋቸው የተከሰሱትን ሌሎች ተጠርጣሪዎችን አቤቱታ እና መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አድምጧል።
ተከሳሾቹ ለችሎቱ እንዳሉት ”ቤተሰብ እይጠየቀን አይደለም። ምግብና ህክምናም በአግባቡ እያገኘን አይደለም። መዝገቡ ሁሉንም ተጠርጣሪዎች በአንድ የያዘ ነው እንደ ኃላፊነታችን መጠን ሊለያይ ይገባል። የዋስትና መብታችን እንዲከበር።” ሲሉ ቅሬታቸውን በጠበቆቻቸው አማካኝነት እቅርበዋል።
በብጥብጡ ወቅት ሞተዋል የተባሉ የ36 ሰዎችን አስክሬን ምርመራ ውጤትን የሚገልጽ ሰነድ ከካራማራ ሆስፒታል መሰብሰቡን፤ የ130 ሰዎችን የምስክር ቃልም መቀበላቸውን፤ ተከሳሾች በሞባይል ስልክ ሲለዋወጡ የነበሩትን መልዕክቶች እንዲመረመሩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ኤጄንሲ/ ኢንሳ/ መላካቸውን፤ የበርካታ ሰዎችም የት እንዳሉ አድራሻቸው ስለማይታወቅ እነሱን የማፈላለግ ስራም እየተከናወነ ነው። በዝርፊያ እና በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶች ግምትም እንዲሰላ ትዕዛዝ መተላላለፉም ፖሊስ ለችሎቱ አሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ፖሊስ ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደረግ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል። የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት አያሰጥም በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል። ችሎቱ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለመስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።