ጥር ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባልፈፀመው ወንጀል በሽብር ክስ ተወንጅሎ በደኅንነት ኃይሎች ከመንገድ ታፍኖ ተወስዶ በእስር ላይ የሚገኘው የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የአራዳ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለ2ኛ ጊዜ የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡
በአራዳ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ምርመራዬን አልጨረስኩም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ያቀረበውን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ለየካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የዋስትና መብቱ ይከበርለት ዘንድ አቶ ዮናታን ተስፋየ ጥያቄውን ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል። ፓሊስ በተከሳሹ ላይ ያልተያዙ ግብረ አበሮቹና የቴክኒክ መረጃዎችን መሰብሰብ ይቀረናል ማለታቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።
ጠበቃው አክለውም ደንበኛቸው በሕገ መንግስቱ የተፈቀደለትን ከጠበቃው፣ከቤተሰቡ ጋር መገናኘት መብቱን መከልከሉንና በታፈነ ክፍል ውስጥ በመታሰሩ የጤና መታወክ ቢደርስበትም ወደ ጤና ማዕከላት እንዳይሄድ መከልከሉን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱም አቶ ዮናታን ያቀረባቸውን አቤቱታዎች አድምጦ በጠበቃውም ሆነ በቤተሰቦቹ እንዲጎበኝ እንዲፈቀድለትና ህክምናም ዕርዳታም እንዲያገኝ ሲል ለእስር ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከችሎቱ ሲወጣ በስፍራው ለነበሩት ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ገልጾ ”ነጻነት ይሰማኛል!›› በማለት ጮክ ብሎ መናገሩን ነገረ – ኢትዮጵያ ዘግቧል።