የቀድሞዋ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የጥፋተኛነት ውሳኔ ተላለፈባቸው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20 2018)

በሙስና ተወንጅለው ወህኒ የወረዱት የቀድሞዋ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት በዛሬው ዕለት የጥፋተኛነት ውሳኔ ተላለፈባቸው።

ውሳኔውን ተከትሎም በ30 ዓመታት እስራት እንዲቀጡ ኣቃቤ ህግ ጠይቋል።

የቀድሞዋ የደቡብ ኮርያ  ፕሬዚዳንት ፓክ ሁን ሄ በሙስና ተወንጅለው ከስልጣናቸው የተባረሩት አምና በመጋቢት ወር ሲሆን ፣ወህኒ ከወረዱም አንድ ዓመት ያህል አስቆጥረዋል።

የ66 ዓመቷ የቀድሞዋ የደቡብ ኮ ርያ ፕሬዳንት ፓክ ሁን ሄ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ያልተገባ ስጦታ ተቀብለዋል፣በሙስና ወንጀልም ተሳትፈዋል እንዲሁም የመንግስት ሚስጥሮችን አሾልከዋል  በሚል ወህኒ ከወረዱበት ግዜ ጀምሮ  በሰንሰለት እየታሰሩም ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ቆይተዋል።በቀረበባቸው ክስ የሴኡል ማዕከላዊ  ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ናቸው ሲልም ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 22/2010  ወሳኔ ሰጥቷል።

ወሳኔውንም ተከትሎ ዓቃቤ ህግ በ30 ዓመታት እስራት እንዲቀጡ የጠየቀ ሲሆን ፣የ110 ሚሊዮን ዶላር  የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸውም ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።አምና በግንቦት ወር የተጀመረው የፍርድ ሂደት ከአንድ ወር በኋላ መጋቢት 28/2010 ፍጻሜ ያገኛል ተብሎም እየተጠበቀ ነው።

በዚህ የሙስና ወንጀል ተባባሪ ናቸው ከተባሉት ተቋማት አንዱ ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ ሲሆን፣የዚህ ኩባንያ ሃላፊ ባለፈው ነሃሴ ወር የ 5 ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል።ሳምሰንግ በዓለም ላይ በሞባይል ቴሊፎን ቴክኖሎጂ ከግንባር ቀደሞቹ አንዱና የጋላክሲ ስልኮች አምራች መሆኑ ይታወቃል።

እ/ኤ/አ በየካቲት ወር 2013 በደቡብ ኮርያ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፓክ ሁን ሄ እ/ኤ/አ መጋቢት 10/2017 በሙስና ቅሌት በሃገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ወሳኔ ከስልጣን ወርደዋል፥ በዚሀም ከቤተ መንግስት በቀጥታ ወደ ወህኔ ቤት ተወስደዋል።የ66 ዓመቷ የየቀድሞዋ  የደቡብ ኮርያ  ፕሬዚዳንት ፓክ ሁን ሄ ትዳርም ሆነ ልጅ የላቸውም። አባታቸው ፓክ ቹን ሂ ደቡብ ኮርያን እ/ኤ/አ ከ1963 እስከ 1979  ለ16 ዓመታት የመሩ የሃገሪቱ ሶስተኛ ፕሬዚዳንት ናቸው።አባታቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት በገዛ የጸጥታ ሃላፊያቸው በመገደላቸው ነበር።