መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በአማራ ጠቅላይ ፍርድቤት ለተመረጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በፍርድ ቤት ዙሪያ ለሚሰሩ ባለሙያዎችና ለመንግስት አመራሮች ባቀረበው የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የቀበሌ ቤትን በተመለከተ የቀረቡ በርካታ አቤቱታዎች ቢኖሩም ፍርድቤቶች አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡ መሆኑን ተሰብሳቢዎችና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ፍርድቤት በኩል ሪፖርት ያቀረቡት ባለሙያ ተሰብሳቢዎች ያቀረቡት አስተያየት ትክክል መሆኑን አምነዋል፡፡የራሳቸውን መኖሪያቤት ከመንግስት ባገኙት ነጻ መሬት የገነቡ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች ቤቱን ላለመልቀቅ የሚያቀርቡት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳለ የገልጹት ባለሙያ ጉዳዩን በጥንቃቄ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ላይ የፍርድቤቶች ውስንነት መኖሩን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
የቀበሌ ቤቶችን ላለመልቀቅ “ጋብቻ አፍርሰናል!” በማለት ፍርድ ቤቱን “ንብረት አከፋፍሉን” የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘው የሚመጡ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የሂደት መሪዎች ጭምር እንዳሉ ባለሙያው ሲገልጹ የያዙትን የቀበሌ ቤቱን ላለመልቀቅ በሐሰት ጋብቻቸውን ያፈረሱ ለማስመሰል የሚያደርጉት አሰራር እንዳለ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ለመስራት ስለሚገደዱ በዚህ ረገድ የቀበሌ አመራሮች የራሳቸውን ስራ በመስራት ችግሩን ከማስወገድ ውጭ ሌላ መፍትሄ እንደሌለው ገልጸው፤ይህንን የአፋቱኝ ጥያቄ በክልል ደረጃ ያሉ አመራሮች እንደሚሳተፉበት ማወቃቸውንና ፍርድቤቶችም ማገዝ እንዳልቻሉ ለተሰብሳቢው ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች የስነምግባረ ብልሹነት ችግር መንሰራፋቱን በተመለከተ ከተሰብሳቢው የቀረበውን አስተያየት እውነት መሆኑን በማመን ንግግራቸውን የጀመሩት ባለሙያ የተሳሰረ የስነምግባር ችግር መኖሩ ከባድ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠበቆች ከዳኛ፣ዳኞች ከአቃቢ ህግ እና ከደላላ ጋር በመመሳጠር ባለጉዳዮችን በሚፈልጉት አቅጣጫ ለመምራት ፍርድቤቶችን ለመቆጣጠርና ለመከራየት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በፍርድቤቶች ዙሪያ እንዳሉ ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡
“ራስን ነጻ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡”የሚሉት ባለሙያ የተወሰኑ ዳኞች በቅብብሎሽ እና በአካባቢያዊነት ተሳስረው የሚሰሩ ስላሉ እነርሱን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ደፍሮ በማጋለጥ በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀት ጊዜው የሚጠይቅ መስዋዕትነት መሆኑን ለሙያ አጋሮቻቸው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡“እንደዚህ ዓይነቱን ስራ ስንሰራ በሃገሪቱ የተንሰራፋው የክራይ ሰብሳቢዎች የበላይነት በመኖሩ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፡፡”የሚሉት ባለሙያው “ክራይ ሰብሳቢዎች ማስረጃ ለማፈን ጉልበት አላቸው፡፡ አንደኛ ጉልበታቸው ሃብት ነው፡፡ በህገወጥነት ያለ አግባብ ባካበቱት ገንዘብ ይጠቀማሉ፡፡ሁለተኛው ጉልበታቸው ስልጣንነው፡፡ በርካታ ጉዳዮችን የሚያበላሹት ስልጣንን ያለአግባብ የሚጠቀሙ በመኖራቸው ነው፡፡”በማለት ችግሩን ለመጋፈጥ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
“በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በርካታ የቀበሌ ቤቶች በመንግስት አመራሮች፣ በስርዓቱ ሰዎችና በባለሃብቶች የተያዙ ናቸው፡፡”የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች“በርካታ ነዋሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በቤት ክራይ በሚሰቃዩባት ሃገር የቀበሌ ቤቶችን በአነስተኛ ገንዘብ ለረዢም አመታት የሚጠቀሙ ባለሃብቶች መኖራቸው የስርዓቱን ፍትሃዊ አለመሆንን ያሳያል፡፡”በማለት እስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን ሰጥተዋል፡፡