የሸጎሌ ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃ ማግኘት ካቆሙ 3 ወራት እንዳለፋቸው ተናገሩ

ጥር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ ሸጎሌ ኪዳነ ምህረት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ዉሃ ከተቋረጠ ሶስት ወራት ማለፉን ተናገሩ።
ወትሮም ቢሆን በ15 ቀናት ዉስጥ አንድ ሌሊት አሳቻ ሰዓት ጠብቆ የሚለቀቀው ውሃ ካለፉት 3 ወራት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። በአካባቢው የሚኖሩ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ከውሃ ጋር በተያያዘ ለሚመጡ በሽታዎች መዳረጋቸውን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታት በሚል በሸጎሌ ድልድይ አካባቢ በላይ ዘለቀ ት/ቤት ጀርባ እና ከጽዮን ሆቴል ጀርባ በተለምዶ ኮካ ሰፈር ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ የዛሬ ዓመት ገደማ ሁለት የከርሰ ምድር ዉሃ የማጎልበት ሰራ የተሰራ ቢሆንም፣ ችግሩ ተባብሶ ከመቀጠል ውጭ መፍትሄ አለመገኘቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡
የዛሬ 4 ዓመት ገደማ አንዲት የቤት ሰራተኛ በእኩለ ሌሊት ከበላይ ዘለቀ ት/ቤት ጀርባ ባለዉ ወንዝ ዉስጥ በተለምዶ “ላቀዉ ምንጭ” እየተባለ በሚጠራዉ ቦታ ዉሃ ወረፋ ለማስያዝ እንደወጣች በጅብ መበላቷን ያስታወሱት ነዋሪዎች፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ፊርማ አሰባስበው አቤት ቢሉም ችግራቸውን ሰምቶ ዘላቂ መፍትሄ የሚፈልግላቸው አካል ማጣታቸውን ለኢሳት ተናግረዋል።