የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የዋጋ ንረትን ማረጋጋት አልቻሉም

መስከረም ፲፬(አሥራ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዋጋ ንረትን ያረጋጋሉ ተብሎ በመንግሥት ልዩ ድጋፍ በተለይ በአዲስአበባ ከተማ የተቋቋሙት የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት በሙስናና ብልሹ አሠራር ውስጥ በመዘፈቅ አንዳንዶቹ

በተቃራኒው የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ሥራዎች ውስጥ መሰማራታቸው መረጋገጡን ከአስተዳደሩ የተገኘ ሰነድ ጠቆመ፡፡ 250ሺ ያህል አባላት ያሉዋቸው 153 መሰረታዊ ማህበራትና 10 ዩኒየኖች እንዲሁም 1 ሺ 815 አዲስ የሸማቾችና ሌሎች

ማህበራት አማካይነት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግስት በድጎማ ጭምር የሚያስገባቸው እንደ ስንዴ፣ ዘይት እና ስኳር ያሉ ምርቶች ከነጋዴዎች ጋር በመሻረክ በማሰራጨታቸው ትርጉም ያለው መረጋጋት በገበያው ላይ ሊታይ ሳይችል ቀርቷል፡፡

ማህበራቱ በ2006 በጀት ዓመት ብቻ ከስኳር ኮርፖሬሽን ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳርና 35ሺ ሊትር ዘይት ለቸርቻሪ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማሰራጨታቸው በሪፖርታቸው የጠቀሱ ቢሆንም ሥርጭቱ የተዛባ በመሆኑ

በገበያው ላይ እነዚህ ምርቶች ገብተው መረጋጋት መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም ብቻ በ482 ማህበራት ላይ በአስተዳደሩ ድጋፍ በተደረገ ኦዲት 4.6 ሚሊየን ብር ጉድለት የተመዘገበ ሲሆን 1.4 ሚሊየን ብር ኪሳራ መመዝገቡን፣

897 ሺ 580 የጎደለ ሐብት እንዲመለስ መደረጉን ተመልክቷል፡፡ ይህን ተከትሎም በአጥፊዎችም ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁሟል፡፡

የአስተዳደሩ ሰነድ አያይዞ እንደጠቆመው ማህበራቱ በንግድ ኢንቨስትመንት፣ በከተማ ግብርናና የህብረት ሥራ ማህበራት ዘርፎች የንግድ ሪፎርሙን ፕሮግራም በመተግበር የንግድ ህጉ ወጥነትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም ፣ኢኮኖሚያዊ ምክንያት

የሌለው የዋጋ ንረት ለመከላከል፣ የነዋሪዎችን ገቢ ለማሳደግ በአንጻሩ ወጪዎቻቸውን ለመቀነስ ያለሙና እርስበእርስ የተሳሰሩ ከመሆናቸውም በላይ ለነዋሪዎች የተደራጀ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የጀመሩ፣ ተደማሪ ውጤቶች

የተመዘገቡባቸው ቢሆኑም አፈጻጸማቸው ወጣ ገባ የሆነና የተለያዩ ጉድለቶች የታዩባቸው ናቸው ሲል ነቀፋውን ያስቀምጣል፡፡

በንግድ አሰራር ስርዓታችን ውስጥ የሚታይና ለኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ያጋለጡ የአመለካከት ማነቆዎች በሁሉም የንግድ ተዋንያን ውስጥ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን በይፋ ያመነው ይህው የአስተዳደሩ ሰነድ የገበያ መሰረተ ከልማት

ማነቆዎች አለመፈታት፣ ለዘመናዊ ንግድ እንቅስቃሴና ህግ ማስከበር ምቹ ሁኔታ አለመኖር እና በህገወጥና ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የተቀናጀ ቅጣት ማሳረፍ አለመቻል አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮች ናቸው ሲል አስቀምጧል፡፡